መግቢያ

ሀገራችን ዋና ጠላታችን የሆነውን ድህነት ለማስወገድ የህዳሴ ጉዞ ቀይሳ መሰረታዊ ለውጥ በሚያመጣ አኳኋን እየተንቀሳቀሰች ትገኛለች። ይህንንም እውን ለማድረግ ሁሉም የሃገሪቱ ክልሎችና የከተማ አስተዳደሮች በሃገር አቀፍ ደረጃ የወጡ ፖሊሲዎችንና ስትራቴጂዎችን በማስፈጸም ድህነትን ማስወገድ እንደ ዋና አጀንዳቸው አድርገው በመረባረባቸው ተጨባጭ ለውጦች እየተመዘገቡ ይገኛሉ። ይሁን እንጂ የዚህ የሀገራዊ ምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ትኩረቱ ገጠር ላይ በመሆኑ በከተሞች ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር በተዘዋዋሪ መንገድ ካልሆነ በስተቀር በቀጥታ ማቃለል አልቻለም። በአንጻሩ ከተሞች ያላቸውንም ዕምቅ ሀብት ባለመጠቀማቸውና በአብዛኛው ሊባል በሚችል ደረጃ ከገጠር በሚቀርቡ የግብርና ምርቶች ላይ ጥገኛ በመሆናቸው የምግብ ዋስትና ችግሮችን በመሠረታዊነት ማቃለል አልቻሉም፡፡ በከተሞች በተለያዩ አካላት እየተካሄዱ ያሉ በመንግስት የሚቀርቡ መሠረታዊ ሸቀጦችና ሌሎች የምግብ ዋስትናን የማረጋገጥ ስራዎችም ለድሃ ተብለው የተቀረፁ ቢሆኑም በአፈፃፀም ረገድ ግን ለታለመለት የማህበራዊ መሰረት የማይደርሱ ናቸው፡፡ ከዚህም በተጨማሪ ስራዎቹ ያልተቀናጁና ያልተናበቡ በመሆናቸው የሀብት ብክነትና የጥገኝነት ስሜት ከማስፈናቸውም ሌላ ዘላቂ ውጤት ማምጣት ላይ ክፍተት ይስተዋልባቸዋል፡፡

የከተሞች ምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ባለመኖሩ ምክንያት የክልል መንግሥታትና የከተማ አስተዳደሮች የየራሳቸውን ፕሮግራምና ፕሮጀክት በመቅረፅ በየአካባቢያቸው ያለውን የምግብ ዋስትና ችግር ተገቢው ትኩረት ሰጥተው ለመፍታት ጥረት ሲያደርጉ አይታይም፡፡ ስለዚህ የከተሞች ምግብ ዋስትና ስትራቴጂ በማዘጋጀትና በዚህም መነሻ ፕሮግራምና የተለያዩ ፕሮጀክቶች በመንደፍ የከተሞቻችን አነስተኛ ገቢ ያለው የህብረተሰብ ክፍል በዝርዝር ለይቶ በጊዜ ገደብ የምግብ ዋስትና ችግር መቅረፍ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም በከተሞች ያለውን የምግብ ዋስትና እጦት ለማቃለልና በዘላቂነት ለማስወገድ ይህን የከተሞች ምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ማዘጋጀት አሰፈላጊ ሆኖ ተገኝቷል፡፡ ይህ ስትራቴጂ በከተሞች የተነደፉትን የከተሞችን ዕድገት በማፋጠን የሚስተዋለውን ድህነትና የምግብ ዋስትና ችግሮች ለማቃለል አልመው የተቀረጹ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞች ልማት ኘሮግራም፣ የቤቶች ልማት ኘሮግራም፣ የከተሞች የአካባቢ ልማት ኘሮግራም፣.....ወዘተ ጋር ሳይቀላቀል በእነዚህ ኘሮግራሞች ችግራቸው ሊፈታ የማይችል የህብረተሰብ ክፍሎች ብቻ ተጠቃሚ ለማድረግ አልሞ የተዘጋጀ ስትራቴጂ ነው፡፡ በመሆኑም የከተሞች ምግብ ዋስትና ስትራቴጂውን መሠረት ተደርጎ የሚቀረጸው ኘሮግራም ድሆችን ብቻ በዝርዝር ለይቶ በተለየ አኳኋን ተጠቃሚ የሚያደርግ ኘሮግራም ማድረግ እጅግ አስፈላጊ ነው፡፡

የምግብ ዋስትና ምንነት

የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ ማለት እያንዳንዱ ዜጋ መጠንና ጥራትን ባማከለ መልኩ በዘላቂነትና ባልተቆራረጠ ሁኔታ ምግብ በማግኘት የነፍስ ወከፍ የዕለት ፍጆታን 2,200 ካሎሪ እንዲደርስ በማድረግ ጤናማና አምራች እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ የምግብ ዋስትና እጦት ስር የሰደደ እና ጊዜያዊ ተብሎ በሁለት ይከፈላል፡፡ ሥር የሰደደ የምግብ ዋስትና እጦት በአብዛኛው በቤተሰብ ደረጃ የጥሪት መመናመንን የሚያመላክት ሲሆን ጊዜያዊ የምግብ ዋሰትና ችግር ደግሞ ድንገተኛ በሆኑ ሰው ሰራሽና ተፈጥሯዊ አደጋዎች የሚከሰት የምግብ አቅርቦት ችግር ነው፡፡

የምግብ ዋስትና ስትራቴጂ የሰው ልጅ የሚያስፈልጉትን መሰረታዊ ፍላጎቶች ለማሟላት የአጭር ጊዜ የምግብ አቅርቦት ችግርን በማቃለል ዜጎችን በቀጣይ ከከፋ ድህነትና ከተመጣጠነ ምግብ ዕጦት ችግር በራሳቸው ጥረት ደረጃ በደረጃ በማላቀቅ ዘላቂነት ባለው መልኩ እንዲቋቋሙና የተሻለ ኑሮን እንዲመሩ የተመቻቸ ሁኔታ የሚፈጥር ነው፡፡ ስትራቴጂው ዝቅተኛ የገቢ ምንጭ ያላቸውንና የመስራት አቅም ያላቸው ዜጎች ከህብረተሰቡ ጋር ሆኖ በጥንቃቄ ከኪራይ ሰብሳቢነት አመለካከትና ተግባር በፀዳ አኳኋን በመለየት ጉልበት፣ ሀብት፣ ክህሎት እና ዕውቀታቸውን አቀናጅተው ኑሯቸውን በዘላቂነት ለመምራት የሚያግዙ እሴትን የሚጨምሩ የአካባቢ ልማት ስራዎችን በስፋት በመስራት በተያያዥነትም ቀጣዩን ኑሯቸውን ሊመሩበት የሚያስችላቸውን ጥሪት በማፍራት መቆጠብ የሚያስችል እና በተደራራቢ የአካል ጉዳት፣ በዕድሜ በጤና ወዘተ ምክንያት በስራ ላይ መሰማራት ለማይችሉ ዜጎች የቀጥታ ድጋፍ የሚሰጥበት ሲሆን ይህም በመንግስት፣ በልማት አጋሮችና በህብረተሰቡ ጥምር ተሳትፎ የሚተገበር ነው፡፡

የምግብ ዋስትና እጦት ተጋላጭነት መንስኤዎች

  1. በስራ ላይ ያለው የታታሪነት መጓደል በከተሞች እየተስፋፋ የመጣውን የስራ አጥነት ችግር ለመፍታት መንግስት በርካታ ፕሮግራሞች ነድፎ እየተንቀሳቀሰ ቢሆንም ከትውልድ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣው ሥራን የማማረጥ አመለካከት ምክንያት የሚሰራ ጉልበትና የሚያስብ አእምሮ ይዘው በሌሎች ጥገኝነት የሚኖሩ ስራ ፈቶች መኖር በከተሞች እየተከሰተ ላለው የምግብ ዋስትና ያለመረጋገጥ አንዱ ምክንያት ነው፡፡ በተለያዩ ኋላቀርና በተሣሣቱ ምክንያቶች አምራች ሊሆን የሚችል ኃይል የተገኘውን ማንኛውንም ሥራ ከመስራት ይልቅ ጎዳና ወጥቶ መለመንን አማራጭ አድርጎ የሚያይ ዜጋ ማስቀረት አልተቻለም፡፡ ይህ አዝማሚያ ደግሞ በዚሁ ከቀጠለ ውሎ አድሮ በህብረተሰቡ ሰላማዊ አኗኗር እና የሃገር ገጽታ ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ ማሳደሩ የማይቀር ነው፡፡
  2. የልማታዊ መልካም አስተዳደር ጉድለት የልማታዊ መልካም አስተዳደር ጉድለት ለምግብ ዋስትና ችግር እንደ አንድ መንስኤ ሲነሳ ስራው የከተማ አስተዳደሮችን ባለቤትነትና ቁርጠኝነት የሚጠይቅ በመሆኑ ነው፡፡ ከተሞች ካላቸው የአስተዳደር ባህርይና የነዋሪዎቻቸው የማህበራዊና የኢኮኖሚያዊ አገልግሎት ፍላጎት ልዩነት ምክንያት ችግሮቹ ውስብስብና ዘርፈ ብዙ ያደርጋቸዋል፡፡ በከተሞች የኪራይ ሰብሳቢነት አስተሳሰብ የበላይነት መያዝ፣ ግልጽነትና ተጠያቂነት ያለው አሰራር በተሟላ አኳኋን ከላይ እስከ ታች ድረስ ያለመዘርጋት፣ የሙስናና ብልሹ አሰራር መገለጫዎች መኖር፣ በሚካሄዱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ሥራዎች የህዝብ ተሳትፎ ውስንነት፣ እንዲሁም ለስራ አጥ ዜጎች በሚደረግ የብድር አቅርቦት እና ተያያዥ ጉዳዮች ላይ የሚታዩት ክፍተቶች... ወዘተ የከተሞቻችን ዋና ዋና የልማታዊ መልካም አስተዳደር ጉድለቶች ናቸው፡፡
  3. የማህበራዊ ጥበቃ ሥርዓት ያለመጠናከር አሁን ካለው ነባራዊ ሁኔታ መገንዘብ እንደሚቻለው የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በመንግስት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም በህብረተሰቡ እየተደረገ ያለው ጥረት በተደራጀ መረጃ ላይ የተመሰረተ ባለመሆኑ፣ እንዲሁም አገር አቀፍ የተጠቃሚዎች ምዝገባ ስርዓት ባለመኖሩ ምክንያት ያለአግባብ የሚደገፉና መደገፍ ሲገባቸው የማይደገፉ ዜጎች ያለበት ሁኔታ ይታያል፡፡ በመረጃ እጥረት ምክንያት የሚከሰተው ፍትሃዊ ያልሆነ የሀብት ተጠቃሚነት መኖር እንዳለ ሆኖ ባልተናበበ አኳኋን የሚደረግ ድጋፍ የጥገኝነት ስሜት ከመፍጠር ያለፈ ዘላቂነት ያለው ዕድገት ሊያመጣ እንደማይችል እሙን ነው፡፡
  4. ከገቢ ጋር ያልተጣጣመ የቤተሰብ ምጣኔ እና የቤተሰብ መላላት የቤተሰብ ምጣኔ አገልግሎት በበቂ ሁኔታ ባለመተግበሩ ምክንያት የቤተሰብ ቁጥር እየጨመረ በመሆኑንና ይህ ደግሞ ከቤተሰብ ገቢ ጋር ባለመጣጣሙ ምክንያት በርካታ የቤተሰብ አባላት ለምግብ ዋስትና ማጣት ተጋላጭ ይሆናሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ዜጎች መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን አሟልተው መኖር ካልቻሉ ለጎዳና ኑሮ፣ ለስደት፣ ለለምኖ አዳሪነት፣ ለሴተኛ አዳሪነት እንዲሁም ለተለያዩ ጎጂ ልማዶች ተጋላጭ የመሆናቸው ዕድል የሰፋ ነው፡፡
  5. የአመጋገብ ባህላችን ያስከተለው አሉታዊ ተጽዕኖ ከአመጋገብ ባህላችን ጋር ተያይዞ በተወሰኑ የእህል ዓይነቶች ላይ ጥገኛ መሆን ለምግብ ዋስትና እጦት የራሱ የሆነ ተፅዕኖ በመፍጠር ላይ ይገኛል፡፡ ለምሳሌ ጤፍን ብቻ ተመራጭ የምግብ ሰብል አድርጎ የማየት ሁኔታ መኖሩ፣ የጤፍ ምርታማነት ከሌሎች ሰብሎች አንፃር አነስተኛ መሆኑና ዋጋውም ከሌሎች የምግብ ሰብሎች ጋር ሲነፃፀር ከፍተኛ በመሆኑ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የሚገኘውን ህዝብ ፍላጎት በበቂ ሁኔታ ማሟላት እየተፈታተነን መሄዱ የማይቀር ነው፡፡
  6. የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ያለመጠናከርና የከተማ ግብርና ለምርት አቅርቦት እያበረከተ ያለው አዎንታዊ አስተዋፅኦ የተጠናከረ ያለመሆኑ የከተማ ግብርና በቤተሰብ ደረጃ የምግብ ፍላጎትን ከሟሟላት ባሻገር ገቢ በማስገኘት ከፍተኛ የሆነ አዎንታዊ አስተዋፅኦ እንዳለው ይታወቃል፡፡ በተለይም ዝቅተኛ ገቢ ያላቸው የከተማ ነዋሪዎች በአነስተኛ መሬት ከፍተኛ ገቢ በሚያስገኙ በከተማ የግብርና ልማት ስራዎች ላይ በመሰማራት የምግብ ፍጆታቸውን ከመሸፈን አልፈው የገቢ ምንጭና ሰፊ የስራ እድል መፍጠር ይችላሉ፡፡ በትምህርት ቤቶች፣ በሃይማኖት ተቋማት፣ መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች፣ በፋብሪካዎች፣ በማረሚያ ቤቶች፣ በወንዝ ዳርቻዎች፣ በተራራዎች፣ በአረንጓዴ ቦታዎች፣ በፓርኮች፣ በህንፃዎች፣ በመንገድ አካፋዮች፣ በግለሰብ ይዞታዎች... ወዘተ ስር ያሉ መሬቶች ለከተማ ግብርና ስራ እንዲውሉ ለማድረግ ያለው ዝግጁነትና ተነሳሽነት ክፍተት ያለበት በመሆኑ ከዘርፉ የሚጠበቀው ውጤት ሊገኝ አልቻለም፡፡

በከተሞች የምግብ ዋስትና እጦት ተጋላጮች

  1. አነስተኛ ገቢ ያላቸው የህብረተሰብ ክፍሎች
    ለአነስተኛ ገቢ መኖር የተለያዩ ምክንያቶች ቢጠቀሱም ዋነኛዎቹ በከተሞች በሚገኘው የሥራ አጥነት ችግር የሚጠቀስ ሲሆን ቁጥሩ ቀላል የማይባል የከተማ ነዋሪ መደበኛ ባልሆኑ ሥራዎች በመሰማራቱ ገቢው ከእጅ ወደ አፍ እንዲሆን አድርጎታል፡፡
  2. ጎዳና ተዳዳሪዎችና ለምኖ አዳሪዎች
    በሃገራችን የተለያዩ ከተሞች በቤተሰብ መላላት፣ መለያየት፣ ፍቺና ሞት፣ የገቢ ማነስ፣ በጓደኛ ግፊት፣ በተለያዩ ሱሶች በመጠመድ ...ወዘተ ምክንያቶች በርካታ ዜጎች በየአካባያቸው የተፈጠረውን መልካም ዕድል አሟጠው ከመጠቀም ይልቅ ውሎና አዳራቸውን ጎዳና ላይ ሲያደርጉ ይስተዋላል፡፡ አብዛኞቹ እነዚህ የጎዳና ተዳዳሪዎች የስነ ልቦናና የክህሎት ስልጠና ቢሰጣቸው ሀገር ገንቢ እና አምራች ኃይል ሊሆኑ የሚችሉ ቢሆንም ተቋማዊና ቀጣይነት ባለው አኳኋን የተሃድሶና የመከላከል ስራዎች የተመቻቹ ባለመሆኑ ምክንያት ህይወታቸውን ጎዳና ላይ በማድረግ ለራሳቸው ስብዕና መጓደልና ለደህንነታቸው አደጋ ከመጋለጣቸውም በላይ በህብረተሰቡና በሃገር ገጽታ ላይ የራሱ ተፅዕኖ መፍጠሩ አልቀረም፡፡ ይህ ማህበራዊ ቀውስ በጨመረ ቁጥር ለሃገር ሠላምና ደህንነት መረጋገጥ ማነቆ መሆኑ አይቀርም፡፡
  3. ሥራ ፈት ዜጎች
    ሀገራችን ባለፉት አሥራ ሁለት አመታት ባስመዘገበችው ባለሁለት አሃዝ ሁለንተናዊ እድገት ምክንያት በርካታ የስራ ዕድሎች እየተፈጠረ መሆኑ ይታወቃል፡፡ በአንጻሩ በከተሞች የኪራይ ሰብሳቢነት የፖለቲካል ኢኮኖሚ በአመለካከትና በተግባር የበላይነት የያዘበት ሁኔታ በመኖሩ እንዲሁም በህብረተሰቡ ውስጥ ሁሉም የተማረ ሰው ተቀጥሮ መስራት እንዳለበት የመፈለግ አስተሳሰብ ቀላል ባለመሆኑ በተፈጠሩ የስራ መስኮች ተሰማርቶ ገቢ ለማግኘት የዝግጁነት መጓደል ይስተዋላል፡፡ መንግስት ይህንን አስተሳሰብ ለመቀየር ሰፊ ሥራ በመስራቱ ከፍተኛ መሻሻል ቢኖርም አስተሳሰቡ ግን አሁንም በተሟላ አኳኋን ተስተካክሏል ማለት አይቻልም፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ህብረተሰቡ ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ በመጣው የተወሰኑ የስራ መስኮችን በፆታ የመመደብ እና ለተወሰኑ የህብረተሰብ ክፍሎች በተፈጥሮ የተሰጣቸው የማስመሰል አስተሳሰብ ስራውንና በስራው ላይ የተሰማሩትን የህብረተሰብ ክፍሎች ተገቢውን የማበረታታት ልምድ ያለመዳበር ይታያል፡፡ ይህም ወቅቱ በፈጠራቸው የስራ ዕድሎች ተጠቅሞ የቤተሰብና የነፍስ ወከፍ ገቢን ከፍ በማድረግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ እንቅፋት ሆኗል፡፡
  4. ልዩ ድጋፍ የሚያስፈልጋቸው የህብረተሰብ ክፍሎች
    በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ምክንያት ወላጆቻቸውን ያጡ ህፃናት፣ ተደራራቢ የአካል ጉዳት የደረሰባቸው የህብረተሰብ ክፍሎች እና ጧሪና ደጋፊ የሌላቸው አረጋውያን ቁጥር ቀላል የሚባል አይደለም፡፡ በሀገራችን ባልተቀናጀ መልኩ በተለያዩ አካላት የሚደረግ የመረዳዳትና የመደጋገፍ ልምዶች ቢኖሩም የተቀናጀና ግልጽ የማህበራዊ ጥበቃ ስርዓት ባለመኖሩ ምክንያት በርካታ የህብረተስብ ክፍሎች መሰረታዊ ፍላጎቶቻቸውን የማሟላት ፈተና ያጋጥማቸዋል፡፡ በዚህም ምክንያት እነዚህ ዜጎች በየጎዳናው፣ በየእምነት ተቋማቱና በቱሪስት መስህብ ቦታዎች ለመለመን መገደዳቸው በራሳቸው ስብዕናና በሀገር መልካም ገጽታ ላይ የራሱ የሆነ አሉታዊ ተጽዕኖ እየፈጠረ ነው፡፡

የከተማዋ የምግብ ዋስትና የማረጋገጥ ውጤታማነት ምስጢሮች

  1. የፖለቲካ ቁርጠኝነት
  2. አጋርነትና የህዝብ ተሳትፎ
    በፕሮጀክቶች ዕቅድና ትግበራ ወቅት መኖር ያለበት ቁርጠኝነትና የማህበረሰብ ተኮር ቡድኖችና ተቋማት ሙሉ ተሳትፎ፡፡ ሁሉም መያዶች፣ ማህበረሰብ ተኮር ተቋማትና ድርጅቶች ፕሮግራሙን አምነውበት እንዲንቀሳቀሱ መደረግ ይኖርበታል፡፡
  3. ትምህርት
    ለፕሮግራሙ ቀጣይነትና ውጤታማነት አስተዋጽኦ ልያደርግ የሚችል ሌላው ጉዳይ ተከታታይ ትምህርት መስጠት ነው፡፡ በተመጣጠነ ምግብ አቅርቦት፣ በአመጋገብ ባህል፣ በምግብ ደህንነት፣ በምግብ አቀራረብና አያያዝ፣ በአካባቢ ጥበቃና ምግብ የማግኘት ሰብዓዊ መብት ዙሪያ በቂ ግንዛቤ እንዲኖር ተከታታይ ትምህርት መስጠት፡፡
  4. ያልተማከለ አስተዳደር
    ፕሮግራሙን ውጤታማ እንዲሆን የሚያደርገዉ ሌላው ጉዳይ ፕሮጀክቶችን እስከ ታችኛው የአስተዳደር እርከን ድረስ በማውረድ መስራት ነው፡፡ በዚህ አሰራር መንግስትና መንግስታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች እንዲሁም ህብረተሰቡ ስራዎችን በግልጽ አቅጣጫና ተጠያቂነት ባለው አሰራር መመራት አለባቸዉ፡
  5. የአካባቢ አስተዳደር ቁርጠኝነትና አመራር
    የአካባቢ የፖለቲካ አመራር ቁርጠኝነት በማሳየት የዜጎች ምግብ የማግኘት መብትን ለማረጋገጥ እንደ ዋነኛው አጀንዳው አድርጎ መውሰዱ ለስኬቱ ቀላል የማይባል አስተዋጽኦ ያደርገጋል፡፡ 27 ቁጥራቸው የተወሰነ የአመራር ቡድኖች፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችና የህዝብ አደረጃጀቶች ቁርጠኛና እልህ የተሞላበት ስራ መስራታቸው የከተማዋ ችግር እንዲቀረፍ አስተዋጽኦ ያደርገጋል፡፡
ለበለጠ መረጃ የከተሞች ምግብ ዋስትና ስትራቴጂ ይጫኑ።

ተያያዥ መረጃዎች
© 2023 Lideta Subcity Job Creation. Designed by Markos Mulat G