መግቢያ

መንግሥት በከተሞች የኢኮኖሚና ማህበራዊ ዕድገትን ለማፋጠን ከቀየሳቸው ስትራቴጂዎች መካከል አንዱ የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ በመሆኑና ስትራቴጂውን በብቃት ለመፈጸም ብቁ የሰው ኃይል፣ ተፈላጊና አዋጭ ቴክኖሎጂ አቅርቦትና የአሰራር ስርዓት ወሳኝ ሚና ያላቸው በመሆኑ፣ በሀገሪቱ የሚገኙ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ገበያን መሠረት ያደረጉ እና በጥራት፣ በምርታማነት፣ በጊዜና በዋጋ ተወዳዳሪ የሆኑ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለማቅረብ እንዲችሉ ፍላጎትን መሠረት ያደረገ እና በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂው በተቀመጠው አቅጣጫ መሰረት የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ለመስጠት የሚያስችል የአሰራር መመሪያ ተዘጋጅቶ ባለፉት አመታት ተግባራዊ በመደረጉ አበረታች ውጤቶች የተመዘገቡ መሆናቸውን መገንዘብ ይቻላል ፡፡

በየደረጃው ያሉ አስፈፃሚ አካላት ማለትም የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ኤጀንሲ፣ የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጄንሲና የአነስተኛ ፋይናንስ አቅራቢ ተቋማት ተቀናጅተው ያላቸውን የሰው ኃይል አቅም በማጐልበትና ሀብታቸውን በማንቀሳቀስ በ2ኛው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ዘመን ብቁና ተወዳዳሪ ኢንተርፕራይዞች ለማፍራት የድርሻቸውን እንዲወጡ ከአዲሱ የኤጀንሲው ተልዕኮ እና ከነባራዊ ሁኔታ ጋር በማገናዘብ ከዚህ ቀደም ይሰራበት የነበረውን የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጥ የነበሩትን ክፍተቶች ለመሙላት በሚያስችል መልኩ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ መሰረት የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ መመሪያ የኢንተርፕራይዞችን የዕድገት ደረጃ እና የኤጀንሲውን ተልዕኮ ታሳቢ ያደረገና ወጥነት ያለው ሞዴል መመሪያ ማዘጋጀት በማስፈለጉ እንዲሁም በዘርፉ የሚሰማሩ ኢንተርፕራይዞች ቁጥር ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገ በመምጣቱ ካለው ነባራዊ ሁኔታ አንጻር ለሁሉም ኢንተርፕራይዞች የሚያስፈልገውን ድጋፍ ከኪራይ ሰብሳቢነት የጸዳ፣ አሳታፊ፣ ፍትሃዊና ውጤታማ በሆነ መንገድ ማቅረብ አስፈላጊ ነዉ ፡፡

ትርጓሜ

1. "የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት" ማለት የኢንተርፕራይዞቹን ችግር የለየና በፍላጎት ላይ የተመሠረተ የተሟላ መረጃ ማደራጀትና የመስጠት፣ ሥልጠና ድጋፍ ፣ የቴክኖሎጂ ልማት፣ ግብይት፣ ምርጥ ተሞክሮ ቅመራና ማስተላለፍን የሚያካትት ድጋፍ ነው፡፡
2. "ሥልጠና" ማለት በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት በንግድ ሥራ አመራርና በቴክኒክና ሙያ የሠልጣኞችን አመለካከት፣ ዕውቀትና ክህሎት የሚያሳድግና በአዎንታዊ መልኩ የባህሪና የአሰራር ለውጥ የሚያመጣ የአጭር የመካከለኛና የረጅም ጊዜ የመማማር ሂደት ነው፡፡
3. "የቴክኒክና ሙያ ሥልጠና" ማለት በጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፎች ለተሠማሩና ለሚሠማሩ የኀብረተሰብ ክፍሎች ፣ ባለሙያዎች አንድን ምርት ወይም አገልግሎት በብቃት ለማቅረብ ፣ ጥራትና ምርታማነትን በቀጣይነት ለማሻሻል፣ የፈጠራ ሥራዎችን ለማበረታታት አመለካከት፣ ዕውቀትና ክህሎት በማሳደግ በተሰማሩበት ወይም በሚሰማሩበት መስክ ላይ እሴትን በመጨመር ልማትን ለማፋጠን እንዲያስችል የሚሰጥ ሙያዊ ሥልጠና ነው፡፡
4. "የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት የድጋፍ ማዕቀፎች" ማለት የቴክኒካል ክህሎት፣ የቴክኖሎጂ ድጋፍ፣ የኢንተርፕሩነርሽፕ እና የጥራትና ምርታማነት/ካይዘን/ ድጋፍ የሚያጠቃልል ድጋፍ ማለት ነው፡፡
5. "ማምረቻ መሳሪያ" ማለት፡- የተለያዩ ጥሬ ዕቃዎችን በመጠቀም ምርትን ለማምረት እና አገልግሎት ለመስጠት የሚያገለግሉ የተለያዩ በሰው ሐይል ፣ በእንሰሳት ጉልበት የሚሳቡ እና በአማራጭ የሃይል ምንጮች የሚሰሩ፣መሳሪያዎችና ማሽነሪዎች ማለት ነው።
6. "የትብብር ስልጠና ስርዓት" " ማለት ሠልጣኙ አብዛኛውን የስልጠና ጊዜ በኩባንያዎች ውስጥ በተግባር እየሰራ የሚሰለጥንበትና ኢንዱስትሪውም ሰልጣኙን በሚፈለገው ደረጃ በማብቃት ለሥራው ብቁ አድርጎ ለማቅረብ የሚቻልበት ዘዴ ሲሆን ተቋማት ከኢንተርፕራይዞች /ቀጣሪ ድርጅቶች ጋር በመሆን በጋራ ጥቅም ላይ የተመሰረተ የትብብር ሥልጠና የሚያካሂዱበት ሥርዓት ነው።
7. "ቴክኖሎጂ ሽግግር" ማለት አንድ የታቀበ ቴክኖሎጂ ፈላጊ ኢንዱስትሪዎችንና አብዥዎችን በመለየትና በማብቃት ቴክኖሎጂውን ከአመንጪዎች ወደ ተጠቃሚዎች የማስተላለፍ ሂደት ነው።
8. "የሙያ ብቃት ምዘና" ማለት አንድ ባለሙያ በተዘጋጀው የሙያ ደረጃ መስፈርት መሰረት የሚጠበቅበትን ብቃት መያዙ የሚረጋገጥበት ስርዓት ነው።
9. "የምርት ሂደት (production process) " ማለት የሰው ኃይል፣ የተፈጥሮ ሃብትና የማምረቻ መሣሪያን በማቀናጀት ጥሬ ሃብትን ወደ ልዩ ልዩ ምርቶች የመቀየ ወይም አገልግሎት የመስጠት እንቅስቃሴ ነው።
11."ምርት (production)" ማለት በማምረት ወይም አገልግሎት በመስጠት እንቅስቃሴ የሚገኝ ተጨባጭ ውጤት ነው።
10. "ጥራት (Quality)" ማለት አንድ ምርት በተጠቃሚው ተፈላጊ የሆኑና እንዲሟሉ የሚጠበቁ ልዩ ልዩ መሥፈርቶችን ሙሉ በሙሉ አሟልቶ የመገኘት ብቃት ነው።
12. "ጠቅላላ ሀብት" ማለት የአንድ ኢንተርፕራይዝ የተከፈለ እና በብድር የተገኘ ሀብት ነው፡፡
13. "ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ" ማለት የኢንተርፕራይዙን ባለቤት፤ የቤተሰብ አባላትና ተቀጣሪ ሰራተኞች ጨምሮ እስከ አምስት ሰዎች ቀጥሮ የሚያሰማራና የጠቅላላ ካፒታሉ መጠን ህንፃን ሳይጨምር በአገልግሎት ዘርፍ ከብር 50,000 (ሃምሳ ሺህ) ወይም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከብር 100,000 (አንድ መቶ ሺህ) ያልበለጠ ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡
14. "አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ " ማለት የኢንተርፕራይዙን ባለቤት፣የቤተሰቡን አባላትና ተቀጣሪ ሰራተኞችን ጨምሮ ከ6 እስከ 30 ሰዎች የሚያሰማራና የጠቅላላ ካፒታል መጠን ሕንፃን ሳይጨምር በአገልግሎት ዘርፍ ከብር 50,001 (ሃምሳ ሺህ አንድ) እስከ 500,000 (አምስት መቶ ሽህ) ወይም በከተማ ግብርና፣ በባህላዊ ማዕድን ማምረትና በግንባታ ዘርፍ ከብር 100,001 (አንድ መቶ ሺህ አንድ) እስከ 1.5 ሚሊዮን ያልበለጠ ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት መርሆዎች

1) የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች መፈልፈያና የቴክኖሎጂ ሽግግር ማዕከላት እንዲሆኑ ማድረግ፣
2) በገበያ ፍላጎት የሚመራ፣ የተቀናጀና የተዋሃደ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት፣
3) ግልፀኝነትን፣ ተጠያቂነትን፤ ታማኝነትን እና ተደራሽትን የተላበሰ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት መስጠት፣
4) የኢንተርፕራይዞች እድገትና ጥቅም የእኔም ጥቅም ነው ብሎ በማመን መንቀሳቀስ፣
5) ለነባርና ሞዴል ኢንተርፕራይዞች ቅድሚያ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት መሰጠት እንዳለበት አምኖ መንቀሳቀስ፣
6) ቴክኖሎጂን መቅዳትና ማሸጋገር ለኢንተርፕራይዞች ቁልፍ የእድገት መሠረት መሆኑንና ለኢኮኖሚ እድገትም ትልቅ መሳሪያ መሆኑን አምኖ መተግበር

የኢንዱስትሪ ኤክስቴሽን አገልግሎት አቅርቦት

የሰው ኃይል ገበያ ጥናት (Labour market analysis)

ሀ) የሰው ኃይል ገበያ ጥናት እንደአስፈላጊነቱ በየዓመቱ የናሙና ዘዴ በመጠቀም በተመረጡ የሥራ ዘርፎችና ነባር ኢንተርፕራይዞች በፌደራልና በክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ኤጀንሲ ይከናወናል፣
ለ) በሰው ኃይል ገበያ ጥናቱ መሰረት ከፌደራል ጀምሮ በየደረጃው የሚገኙ የከተማ የስራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ጽ/ቤቶች በተዋረድ በጥቃቅን አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ዘርፍ የሚሰማራውን የሰው ኃይል በሙያ፣ በደረጃና በብዛት በመለየት አዘጋጅተው ለቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና ተቋማት ይሰጣሉ፡፡
ሐ) ሙያዎችን የመለየትና ሃገር አቀፍ የሙያ ደረጃዎችን የማዘጋጀት ተግባር በፌደራል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ሥልጠና አመቻችነት ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን ጨምሮ በሥራ ዓለም ያሉ ባለድርሻዎችና በየኢንዱስትሪ ዘርፉ ባለሙያዎች መሪነት ይከናወናል። ዓለምአቀፍ ምርጥ ተሞክሮዎችና የሙያ ደረጃዎች በግብዓትነት ይወሰዳሉ።
መ) በተዘጋጀው የሙያ ደረጃ መሰረት የክልል የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ቢሮ/ኤጀንሲ ተቋማት የከተሞች የስራ ዕድል ፈጠራ እና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲን በማሳተፍ ስርዓተ ትምህርትና የማሰልጠኛ ማንዋል ያዘጋጃሉ።
ሠ) ነባር ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞችን በተዘጋጀው የሙያ ደረጃ መሰረት የሙያ ብቃት ምዘና እንዲያገኙ ማድረግ ክፍተታቸውን ለይቶ ማብቃት፣

የስልጠና አገልግሎት ተጠቃሚ ለመሆን የሚያበቁ መስፈርቶች

ሀ) በሥልጠና ፍላጎት ጥናት መሰረት የተለየ፣
ለ) በግልም ሆነ በማህበር ለመሰልጠን ፍላጎት ያለውና ጥያቄውንም በማመልከቻ የሚያቀርብ፣
ሐ) ስልጠናው የሚጠይቀውን የትምህርት ዝግጅትና የሥራ ልምድ ያሟላ፣
መ) በሥልጠና ያገኘውን እውቀትና ክህሎት ሥራ ላይ ለማዋል ዝግጁ የሆነ፣
ሠ) በተዘጋጀው የሙያ ደረጃ መሰረት የብቃት ማረጋገጫ ምዘና ለመውሰድ ፍቃደኛ የሆነ

የሚሰጡ የሥልጠና ዓይነቶች

የኢንተርፕረነርሽፕና የንግድ ሥራ ክህሎት ስልጠና

ሀ) ለጀማሪ ኢንተርፕራይዞች

(1) አደረጃጀት
(2) ንግድዎን ይጀምሩ
(3) መሰረታዊ ኢንተርፕረነርሽፕ
(4) መሰረታዊ የሒሳብ መዝገብ አያያዝ
(5) መሰረታዊ የወጪ ማስላትና ዋጋ ተመን
(6) መሰረታዊ ንብረት አያያዝ
(7) መሰረታዊ ገበያ አያያዝ
(8) የንግድ ስራ ዕቅድ አዘገጃጀት
(9) ብቃት ያለው የንግድ ሰው ማዘጋጀት (CEFE)

ለ) ለታዳጊ ኢንተርፕራይዝ

(1) ንግድዎን ያሻሽሉ፣
(2) የደንበኛ አያያዝ፣
(3) የሰው ኃይል ስራ አመራር፣
(4) የሒሳብ መዝገብ አያያዝ፣
(5) የወጪ ማስላትና ዋጋ ተመን፣
(6) መሰረታዊ የጥራትና ምርታማነት ሥራ አመራር (ካይዝን)፣

ሐ) ለበቃ ኢንተርፕራይዝ

(1) ንግድዎን ያሻሽሉ፣
(2) የደንበኛ አያያዝ፣
(3) የሰው ኃይል ስራ አመራር፣
(4) የሒሳብ መዝገብ አያያዝ፣
(5) የወጪ ማስላትና ዋጋ ተመን ፣
(6) ከፍተኛ የጥራትና ምርታማነት ሥራ አመራር(ካይዝን)፣
(7) ISO የጥራት ስራ አመራር ስርዓት፣

ተፈላጊና አዋጭ የቴክኖሎጂ ልማትና አቅርቦት

በኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂ ውስጥ የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርኘራይዞች የኢንዱስትሪ ልማታችንን በብቃት መደገፍ እንዲችሉና ተወዳዳሪነታቸውን ለማሳደግ በቴክኖሎጂ አቅርቦት የታገዘ የኤክስቴንሽን አገልግሎት ሊያገኙ ይገባል፡፡

ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ሊያገለግሉ የሚችሉ ቴክኖሎጂዎች ከሚከተሉት ምንጮች ሊገኙ ይችላሉ

(1) ከቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት፣
(2) ከቴክኖሎጂ ድጋፍ ኢንስቲትዩቶች፣
(3) ከዩኒቨርሲቲዎች፣
(4) ከገጠር ቴክኖሎጂ ማስፋፊያ ማዕከላት፣
(5) ከአስመጪዎች፣
(6) ከከፍተኛና መካከለኛ ፋብሪካዎች፣
(7) ከነባር ኢንተርፕራይዞች፤
(8) ከድረ ገጽ (ኢንተርኔትና ከሌሎች ምንጮች) ማሰባሰብ፣

የጥራትና ምርታማነት /ካይዘን/ አገልግሎት

የጥራትና ምርታማነት/ካይዘን/ አገልግሎት የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ብክነትን በመቀነስ በሥራቸው ትርፋማ እንዳይሆኑ መሰናክል የሆኑባቸውን የአመራርና አሰራር ችግሮችን ለመፍታት የሚሰጥ ድጋፍ ነው፡፡ በዕድገት ተኮር የሥራ ዘርፍ የተሰማሩ ጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች እንደየእድገት ደረጃቸው የንግድ ሥራቸውን ለማሳደግ እና ብክነትን በመቀነስ የሚያመርቱት ምርት በገበያ ተወዳዳሪ እንዲሆን ለማድረግ የጥራትና ምርታማነት/ካይዘን/ አገልግሎት ከፍተኛ ሚና አለው::

በካይዘን አገልግሎት ውስጥ የሚከናወኑ ዋና ዋና ተግባራት

ሀ) ስለካይዘን አገልግሎት አስፈላጊነት የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራ መሥራት፣ ለ) የጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያሉባቸውን ውስጣዊና ውጫዊ ችግሮች በመለየትና ላጋጠሟቸው ችግሮች ተጨባጭ መፍትሔ በመስጠት ኢንተርፕራይዞቹን ተወዳዳሪ ለማድረግ በሚያስችል ሁኔታ በተደራጀና በተቀናጀ መልኩ የማማከር አገልግሎት እና ተግባር ተኮር ስልጠና እንዲሰጥ ማድረግ፣

የጥራትና ምርታማነት ድጋፍ ተጠቃሚዎች ማሟላት ያለባቸው መስፈርት

ሀ) የድጋፍ ተጠቃሚ ለመሆን በራስ ተነሳሽነት ጥያቄ ማቅረብ፣
ለ) ለድጋፍ አስፈላጊ የሆኑ ተአማኒነት ያላቸው መረጃዎችን ለመስጠት ዝግጁ የሆነ፣
ሐ) ከአሰልጣኝ የሚሰጠውን የሥራ ድርሻ ለመተግበር ዝግጁና ፍቃደኛ የሆነ፣
መ) የድጋፍ አገልግሎት ጥቅም በአግባቡ የተረዳ ፣
ሠ) በተሰማራበት ወይም ሊሰማራ ባሰበበት የሥራ መስክ በልምድ ወይም በትምህርት የተገኘ ተጨበጭ ክህሎትና እውቀት ያለው መሆን አለበት፣

የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ባለሙያዎች /የአሰልጣኞች/ ዋነኛ የሥራ ድርሻ

1) ለጥቃቅን እና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ያሉባቸውን የኢንተርፕርነርሺፕ፣ የሂሳብ አያያዝ፣ የፋይናንስ፣ የገበያ ችግሮች ለማቃለል ሁሉ አቀፍ የምክር አገልግሎት ድጋፍ መስጠት፣
2) በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ፣ የምክር አገልግሎት እንዲሁም በአገልግሎቱ ተጠቃሚነት ላይ ግንዛቤና የማነሳሳት ስራ መስራት፣
3) የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ መረጃዎች፣ የፋይል አደረጃጀት ስልት ለእያንዳንዱ ድጋፍ ተቀባይ ኢንተርፕራይዝ ወይም ግለሰብ የነባራዊ ሁኔታ ትንተና (situation analysis) ፎርማቶች በመጠቀም በተገቢው ማደራጀት፣
4) ከአገልግሎት ተቀባዩ ጋር የተግባር መርሃ- ግብር (Action planning) ማዘጋጀት፤
5) በድርጊት መርሃ ግብሩ መሠረት ኢንተርፕራይዙ ተገቢውን ድጋፍ ማግኘቱን ማረጋገጥ እና የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን የተሰጠበትን ሪፖርት ማዘጋጀት፣ የአገልግሎት ተጠቃሚዎችን ዝርዝር መረጃ ለዚሁ አላማ በተዘጋጀዉ መዝገብ/Journal/ ላይ መመዝገብ፣
6) ኢንተርፕራይዞቹ የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ በማግኘታቸው ያመጡት ለውጥ በተከታታይ መገምገም፣ ችግሮችም ማስተካከል፣
7) ለኢንተርፕራይዞች የተሰጡት የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ በሙያ ብቃት ምዘና ማረጋገጥ፡
8) የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አሰልጣኝ ከላይ በዝርዝር የተቀመጡትን ተግባራት ባይፈጽም ሙሉ ተጠያቂ ይሆናል፡፡

የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት አሰጣጥ ዘዴ

1) በግል ወይም በንግድ ማህበር ለተደራጁ ኢንተርፕራይዞች በሥራ ቦታ በመገኘት ወይም ጉብኝት በማድረግ የንግድ ልማት ምክር አገልግሎት መስጠት፣
2) በተመሳሳይ የሥራ መስክ ተሰማርተው የሚገኙ ኢንተርፕራይዞች በልማት ቡድን በማደራጀት በሥራ ቦታቸው በአካል በመገኘት ወይም በክላስተር ማዕከል መደበኛ የንግድ ምክር አገልግሎት መስጠት፣

ምርጥ ተሞክሮዎችን መቀመርና ማስፋት

በኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት የላቀ ውጤት ያመጡ ኢንተርፕራይዞችን ውጤታማ እንዲሆኑ ያስቻላቸውን የዕቅድ፣ የአፈፃፀምና የአሠራር ልምድ በማደራጀትና በመቀመር ምርጥ ተሞክሮዎችን በመለየት በስልጠና፣ በልምድ ልውውጥና በንግድ ልማት ምክርና በካይዘን አገልግሎት ወደ ሌሎች ኢንተርፕራይዞች በማሸጋገር የተሳካ ውጤት እንዲያመጡ በቅርበት ክትትል እና ድጋፍ ይደረጋል፡፡

የምርጥ ተሞክሮ መቀመሪያ መስፈርቶች (ቼክ-ሊስት)

ሀ) ሞዴል ኢንተርፕራይዙ ያሉበትን ችግሮች በራሱና በሚሰጠው ድጋፍ የፈታበት አግባብ እንዴት መለየት እንደቻለ፤
ለ) የተለዩ ችግሮችን ለመፍታት የተደረገለት የማምረቻ መሣሪያ፣ የንግድ ልማትና ካይዘን አገልግሎት፣ የቴክኖሎጂ ልማትና ስልጠና ድጋፍ በውጤታማ መንገድ እንዴት እንደተጠቀመ፣
ሐ) እንዴት ልማታዊ አሰተሳሰብ ሊያሳድግ እንደቻለ፤
መ) የሥራ ክህሎት አጠቃቀም፤
ሠ) በገበያ ውስጥ በምርት ጥራትና በዋጋ እንዴት ተወዳዳሪ መሆን እንደቻለ፣
ረ) በገበያ የሚፈለገው የምርት ጥራትና ስታንዳርድ እንዴት ሊጠብቅ እንደቻለ፣
ሰ) እንዴት ውጤታማ ተቋማዊ አመራርና አደረጃጀት በስራ ላይ እንዳዋለ፣
ሸ) ምርታማነቱን እንዴት እንዳሳደገ፣
ቀ) የሚሰጡ መንግስታዊ ድጋፎችንና አገልግሎቶችን በአግባቡ መጠቀም እንዴት እንደቻለ /ብድር፣ ማምረቻ ቦታ፣ ገበያ/፤
በ) ያለውን የገበያ ድርሻ እንዴት እንዳሳደገ፣
ተ) ለተከታታይ ዓመታት እንዴት ትርፋማ መሆን እንደቻለ፣
ቸ) ካፒታል እንዴት እንዳሳደገ፣
ኀ) ለሌሎች የስራ ዕድል መፍጠር እንዴት እንደቻለ፣
ነ) በኢንተርፕራይዙም ሆነ በተቀጣሪ ሠራተኞች ዘንድ እንዴት ቁጠባን ሊያሳድግ እንደቻለ ያካተተ ይሆናል፡፡

ለኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎት የሚያስፈልጉ ግብዓቶች

የሰው ኃይል

የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ሥራ መረጃ የማደራጀት፣ የሰው ኃይል ልማትን፣ የቴክኖሎጂ መረጣና አቅርቦት፣ የግብይት ማበልጸጊያ፣ የሂሳብ መዝገብ ዝርጋታ፣ የኢንተርፕርነርሽፕና የንግድ ሥራ ክህሎት እና የካይዘን ተግባራትን ያካተተ በመሆኑ በየደረጃው የሚደራጀው መዋቅር እንደአስፈላጊነቱ ተግባሩን በብቃት ለማከናወን እንዲችል እንደየ ኢንተርፕራይዞቹ እድገት ደረጃ ከዚህ በታች በተዘረዘሩት መመዘኛዎች መሰረት የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት አሰልጣኞች አገልግሎቱን ይሰጣሉ፡፡
ሀ) ከኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ጋር አግባብነት ያለው የትምህርት ደረጃና የሥራ ልምድ ያላቸው፣
ለ) በቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ስትራቴጂ፣ በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት ስትራቴጂ እና የአገልግሎት የአፈጻጸም ስርዓት ላይ ስልጠና ያገኙና በቂ ግንዛቤ ያላቸው፣ ሐ) በንግድ ልማትና በካይዘን አገልግሎት ሥልጠና ያገኙ፣
መ) የንግድ ልማት አገልግሎት በሚያካትታቸው መስኮች (በግብይት ስርዓት፣ በፋይናንስ ድጋፍ፣ በኢንተርፕርነርሽፕ፣ የሂሳብ አያያዝ ዝርጋታ፣ በመረጃ፣ በንግድ ዕቅድ ዝግጅት፣ በቴክኖሎጂ ልማት) ስልጠና ያገኙ፣
ሠ) በዘርፉ ለውጥ ለማምጣት የሚደረገውን ጥረት ለመደገፍ ጠንካራ ተነሳሽነትና ጥሩ ስነ- ምግባር ያላቸው፣

ቁሳዊ ግብዓቶች

በየደረጃው የሚሰጡትን አገልግሎቶች በተሟላ አኳኋን ለማቅረብ ለሥራው ተፈላጊ ቁሳዊ ግብዓቶች ሊሟሉ ይገባል በመሆኑም፣
ሀ. የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ ቀጣይነት ያለው እንዲሆንና የጥራትና ምርታማነት ማሻሻያ ሥራ አመራር (KAIZEN) እና ለመረጃ አያያዝና ስርጭት አገልግሎት የሚያስፈልጉ ቁሳዊ ግብዓቶች መሟላት ይኖርበታል።
ለ. ለሰው ኃይል ሥልጠናና ለቴክኖሎጂ አቅርቦት ድጋፎች የሚውሉ ወርክሾፖች እንደሙያ ዘርፉ በተሟላ የማሰልጠኛና ማምረቻ መሣሪያዎች፣ ማሽነሪዎችና መገልገያዎች እንዲደራጁና እንዲሟሉ ይደረጋል።
ሐ. ለኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን ድጋፍ ለሚወጡ አሰልጣኞች የትራንስፖርት አማራጮችን ማመቻቸት፡፡

የፋይናንስ አቅርቦት

የኢንዱስትሪ ኤክስቴንሽን አገልግሎትን በብቃትና በጥራት ለመስጠት እንዲቻል በየደረጃው የሚገኙ ፈጻሚ አካላት አስፈላጊውን በጀት ዕቅድ በመያዝ ደረጃ በደረጃ ለኤክስቴንሽን አገልግሎቱ ግብዓቶች ማሟላት ይጠበቅባቸዋል፡፡

ተያያዥ መረጃዎች
© 2023 Lideta Subcity Job Creation. Designed by Markos Mulat G