መግቢያ

በአገራችን ፈጣንና ቀጣይነት ያለው ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ልማት እውን ለማድረግ የመንግስት ተቋማትን የማስፈጸም አቅም ግንባታን ቁልፍ ተግባር በማድረግ እየተሰራበት ይገኛል፡፡ በዚህ ረገድ በከተማችን የተጀመረው ዘርፈ ብዙ የለውጥ አፈጻጸም እንቅስቃሴ ውጤታማነት በዘላቂነት ጠብቆ ለማቆየት እንዲያስችል በየሂደቱ ያሳካናቸውንና ያስመዘገብናቸውን የልማት፣ የሰላምና የዲሞክራሲና የመልካም አስተዳደር ምርጥ ተሞክሮችን በመለየት፣ በመቀመርና በማስፋት የላቀ ውጤት ማስመዝገብ የምንችልበትን አቅጣጫ በመከተል ዕቅዶቻችንን ተግባራዊ ማድረግ ይጠበቅብናል፡፡

በመሆኑም የመንግስት ተቋማት የለውጡን ትግበራ ከእድገትና የትራንስፎርሜሽን ዕቅድ ጋር በማዋሃድ ተገልጋይ ተኮር፣ ፈጣን፣ ተደራሽና ውጤታማ በሆነ መልኩ ተግባራዊ ማድረግ እንዲያስችላቸው ስልት በመቀየስ በአፈፃፀማቸው የተሻለ ደረጃ ላይ የደረሱ ተቋማት ምርጥ ተሞክሮ በመቅሰም ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ጋር በማስማማት ተግባራዊ ማድረግ የሚያስችላቸው አቅም መፍጠር የሚያስገኘው ፋይዳ የጎላ ነው፡፡ ስለሆነም ይህን የለውጥ ጅምር ቀጣይነት ባለው መልኩ በየደረጃው ለማረጋገጥና ይበልጥ ለማቀጣጠል በተግባር አፈጻጸማቸው ውጤታማ የሆኑና ወጣ ባለ ደረጃ ላይ የሚገኙ ክ/ከተሞችና የወረዳ ተቋማት ተሞክሮዎችን ለይቶ በመቀመር ወደ ሌሎች ማስፋት አማራጭ የሌለው ተግባር ነው፡፡

ትርጓሜ

ምርጥ ተሞክሮ ማለት ዕቅድን በማዘጋጀትና በመተግበር ረገድ በተወሰኑ አካባቢዎች ስኬታማነታቸው የተረጋገጡ፤ የትኞቹ ሊተገበሩ እንደሚችሉና የትኞቹ ሊተገበሩ እንደማይችሉ፤ እንዲሁም በተለያዩ ሁኔታዎችና አውዶች ውስጥ እንዴትና ለምን እንደሚሰሩ ዕውቀት ለማካበትና በሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ልምድ ነው
"ምርጥ ተሞክሮ" “….ከመጠንና ከጥራት አንጻር ስኬታማነቱ የተረጋገጠ አንድ ወይም የተለያዩ ሥራዎች ለመባዛት፣ አላምዶ ለመጠቀምና ለሌሎች ለማስተላለፍ የሚቻሉ መሆናቸውን ያመላክታል፡፡ ምርጥ ተሞክሮዎች የተቀመጠውን ከፍተኛ ደረጃ “Gold standard” የሚያሟሉ ተግባራትና መሳሪያዎች ሲሆኑ የፕሮግራም ግቦችን ለመደገፍ በሥራ ላይ የሚውሉ ናቸው፡፡
"ምርጥ ተሞክሮ" ለአንድ ድርጅት አፈጻጸም መሻሻል አስተዋፅኦ ያበረከቱ ብልጫ ያለውን ዘዴና ፈጠራ የተሞላበት ተግባር የሚያሳይ እና ይህም በአብዛኛው ተመሳሳይ ድርጅቶች እውቅና የተቸረው ብልጫ ያለው ልምድ ነው፡፡ ይህም በተለያዩ ሁኔታዎችና አውዶች ውስጥ የትኞቹ ምርጥ ተሞክሮዎች ሊተገበሩ እና የትኞቹ ደግሞ በሥራ ላይ ሊውሉ እንደማይችሉ፤ ከእነዚህም የተማርናቸው ትምህርቶች፣ በሂደት የምንማራቸው፣ ግብረ መልስ፣ ምን እንዴትና ለምን እንደሚሰራ መጠየቅና መተንተን የሚገቡንን ጉዳዮች አካቶ የያዘ ልምድ ነው፡፡

ስለሆነም የምርጥ ተሞክሮ ጽንሰ ሃሳብ ሲታይ ከጥሩ ምሳሌዎች፣ ከመልካም ልምዶች፣ ከሥኬታማነት ምንጭነት፣ ከግንባር ቀደም ተጠቃሽ ተግባራት ወ.ዘ.ተ ጋር የመመሳሰል ትርጉም አለው፡፡ ምርጥ ፍጹምነትን ወይም የጥራት ደረጃን የሚወክል ሳይሆን ሥኬትን ለማምጣትና ችግሮችን ለመፍታት የተጠቀምንበት ስልት ጥቅም ላይ የሚውልበት ቴክኒካዊ የአሰራር ቅደም ተከተል ነው፡፡
ስለሆነም የታዩ ተጨባጭ ለዉጦችንና ዉጤታማነታቸዉ የተረጋገጠላቸዉ ምርጥ ልምዶችን ወደ ሁሉም ሴክተሮች ለማዳረስ በሚገባ ተቀምሮና ከከተማዉ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ተቃኝቶ እንዲሰፋ የማድረግ ተግባር ነዉ፡፡

የምርጥ ተሞክሮ ጠቀሜታ

ምርጥ ተሞክሮን በመለየት አካትቶ መጠቀም ለአንድ ተቋም ስኬታማነት ከፍተኛ አስተዋጽዖ አለው፡፡ ምርጥ ተሞክሮን ሥራ ላይ በማዋል ሊገኝ የሚችል ጥቅም እንደሚከተለው ተገልጿል፡፡
  1. የተጠቃሚውን ህብረተሰብ ወይም የደንበኛን ጥያቄ መሰረት ያደረገ የተሻሻለ እና ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት ይረዳል፣
  2. ምርታማነትን እና ቀልጠፋነትን /Effeciency/ ይጨምራል፣
  3. የደንበኛን ፍላጐት መሠረት በማድረግ የአገልግሎት መጠንን ለማሳደግ/አገልግሎትን ተደራሽ ለማድረግ/ ይረዳል፣
  4. ኋላቀር አሰራርን በመለየት የተሻሻለ አሰራር ሊያመጣ የሚችል ስትራቴጂና ፕሮግራም ለመንደፍ ይረዳል፣
  5. ስኬታማ ለመሆን እንዲቻል የህዝብ እና የግል ሴክተርን በማሳተፍ የተቋሙን ፋይናንስ አቅም ማሳደግ ይረዳል፣
  6. ውስን ሃብትን ወጪ ቆጣቢ በሆነ መልኩ በመጠቀም የግብ ስኬትን ማምጣት ያስችላል፤
  7. የአመራሩንም ሆነ የፈፃሚውን አቅም ለማሳደግ ይረዳል፣

በምርምር የተረጋገጡ ምርጥ ተሞክሮዎች ዓይነትና መለያ መስፈርት/Research Validated best practice/

ውጤታማነታቸው በተጨባጭ መረጃ ላይ የተመሰረተ እና ሁሉንም ባካተተ መልኩ በምርምር የተረጋገጡ ፕሮግራሞች፣ ፕሮጄክቶች፣ዋና ዋና ተግባራቶችና ስትራቴጂዎች ናቸው፡፡
የመለያ መስፈርት
• የጋራ የሆኑ ችግሮችን በመፍታት ውጤታማነቱ የተረጋገጠ፤
• በከፍተኛ ደረጃ አስፋፍቶ መጠቀም የሚቻል መሆኑ፤
• ተሞክሮዎችን ከማወዳደር ጀምሮ በተግባር ውጤት እስከሚያመጡበት ድረስ የተገኙ መረጃዎች በዕውነት ላይ የተመሠረቱ መሆናቸው፤

በተግባር የተፈተሹ ምርጥ ተሞክሮዎችና መለያ መስፈርት /Field tested best practice/

በሥራ ላይ ውለው ስኬታማ ውጤት ያስገኙ ፕሮግራሞች፣ተግባሮች ወይም ስትራቴጂዎች ናቸው፡፡ • የጋራ ችግሮችን በመፍታት ውጤታማ የሆነ፤
• ከአንድ በላይ በሆኑ ተቋማት እና በተለያዩ ሂደቶች ውጤታማ የሆነ፤
• በተሰበሰበው መረጃ መሠረት የተገኘው ውጤት ከተቀመጠው ስታንዳርድ ጋር ሲወዳደር የተሻለ ሆኖ ከተገኘ፤
• በውስጥ ወይም በዉጫዊ አካል ተግምግሞ ውጤታማነቱ በመረጃ የተረጋገጠ፤

በትግበራ ላይ ያሉና ተስፋ ሰጪ ምርጥ ተሞክሮዎች /Promising best practice/

በአንድ ተቋም/ሴክተር ውስጥ በሥራ ላይ የዋሉ ፕሮግራሞች፣ተግባሮች ወይም ስትራቴጂዎች ሲሆኑ በመጀመሪያ የሙከራ ጊዜ ላይ ተስፋ ሰጪ ውጤት እየሰጡ ያሉና በረጅም ቆይታ አስተማማኝና ዘላቂነት ያለው ውጤት የሚያመጡ ናቸው፡፡ ይህ የተሞክሮ ዓይነት በተጨባጭ ውጤት ላይ የተመሠረተ እና በሌሎች ሴክተሮች ሊስፋፋ የሚችል መሆን አለበት፤
የመለያ መስፈርት

  • የጋራ የሆኑ ችግሮችን ከመፍታት አኳያ ውጤታማ ስለመሆናቸው አስተያየት የተሰጠባቸው፤
  • በተቋም/ሴክተር ደረጃ እና በሥሩ ባሉት አደረጃጀቶች ጥቅም ላይ ውሎ ስኬት የተገኘበት፤
  • ወደ ሌሎች ለመስፋት ብቃት ያለዉ፤
  • የምርጥ ተሞክሮ መገለጫ ባህርያት

    የምርጥ ተሞክሮ መገለጫ ባህሪያት በተለያየ መልኩ የተለያዩ ባለሙያዎች የገለጹ ቢሆንም ስምምነት የተደረሰባቸው ሰባት ዋና ዋና የምርጥ ተሞክሮ ባህሪያት ለማስቀመጥ ተሞክሯል፡፡
    1) የለውጡ አድማስ ሠፊ መሆን
    የለውጡ አድማስ ሠፊ የሆነ ሲባል ለውጡ በሁለት፣ በሶስት፣ በአራት እጥፍ የሚንፀባረቅ የሚጨበጥና የሚዳሠስ፤ በተወሰኑ ቦታዎች ወይም ጥቂት የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ብቻ ሳይሆን በቀጥታም ሆነ በተዘዋዋሪ ሠፋ ወዳለ አካባቢ እና የህብረተሰብ ክፍል ሊዳረስ የሚችል ለውጥ ማለት ነው፡፡
    2) ከፍተኛ የጥራት ደረጃ ያለው
    አንድ ልምድ በምርጥ ተሞክሮነት የሚወሰድ ከሆነ ቢያንስ ከተቋማት መካከል ጥራት ያለው ምርት ወይም አገልግሎት በመስጠት በተሻለ ደረጃ ውጤት ያመጣ መሆን ይገባዋል፡፡ በመሆኑም በአንድ አካባቢ ወይም ተቋም ምርጥ ልምድ አለ ለማለት ቢያንስ በጥራት ደረጃው በሌሎች ሊመሰከርለት የሚችል ሆኖ መገኘት አለበት።
    3) በቀላሉ የመስፋፋት ዕድል ያለውና ልዩነት የሚፈጥር መሆኑ
    በምርጥ ተሞክሮነት የሚወስድ ልምድ በቀላሉ የመስፋፋት ዕድል ያለውና በተለያዩ ምክንያቶች የማይስተጓጎል፤ ሲተገበርም በተጨባጭ ልዩነት የሚፈጥርና አወንታዊ ተጽዕኖ የሚያሳድር መሆን አለበት፡፡
    4) የፈጠራ አሰራር የታከለበት አሰራር መሆኑ
    አዳዲስ አሰራሮችን በመዘርጋት በተቋም ወይም በአካባቢ ውስጥ በተደጋጋሚ ለሚያጋጥሙ ችግሮች የራስ ፈጠራን በመጠቀም ለችግሮቹ መፍትሄ በመስጠት የላቀ ውጤት የሚገኝበት መሆን ይገበዋል፡፡
    5) በአቅማችን ልንተገብረውና ደጋግመን ለመጠቀም ተጨማሪ ወጪ የማያስወጣን ሊሆን የሚገባው መሆኑ፣
    ምርጥ ልምድ በመጠቀም ስርነቀል ለውጥ በዘላቂነት ማምጣት የሚቻለው አቅምን ያገናዘበ (affordable) እና ቀጣይነት ያለው (Sustainable) ሆኖ ከተገኘ ብቻ ነው፡፡ ስለዚህ ምርጥ ልምዶችን ለማስፋት ከወጪ አንፃር አዋጭና የተቋማትን አቅም ያገናዘበ መሆኑን መፈተሽ ተገቢ ይሆናል፡፡
    6) ፈጣንና ስር-ነቀል ለውጥ የሚያመጣ መሆኑ፣
    የምርጥ ተሞክሮ ሌላው ባህርይ በአጭር ጊዜ ፈጣንና የማይታመን የሚመስል ለውጥ በጥቂት ጊዜ ውስጥ የሚገኝና ውጤቱ የሚታይ፤ እንዲሁም በተመሣሣይ አመት የሚፈጀው በወራት በቀናት ማረጋገጥ ማስቻሉ ነው፡፡ በመሆኑም ስለምርጥ ተሞክሮ ስንነጋገር ለውጡ እጅግ ፈጣንና በአጭር ጊዜ እውን ሊሆን የሚችል፤ ይህም ሲባል በሌሎች አካባቢዎች ለውጥ ወይም ውጤት ለማምጣት ረጅም ጊዜ የፈጀውን በአጠረ ጊዜ ውስጥ ለውጥና ውጤት ሊያመጣ የሚያስችል ምርጥ አፈፃፀም ማለት ነው፡፡
    7) የግብ ስኬቱ ሊቀለበስ የማይችል መሆኑ፣
    ስርነቀል ለውጥ የሚያመጣ ምርጥ ተሞክሮ ሲባል ለአጭር ጊዜያት ቆይቶ ውጤት የሚያስገኝ እና በማግስቱ የሚፈራርስ ወይም የሚተን አይደለም፡፡ ይልቁንም በፅኑ መሰረት ላይ የተገነባና ለረዥም ጊዜያት የሚቆይ ፋይዳ ያለው ለውጥ ማለት ነው፡፡ ፋይዳው የማህበራዊ አኗኗርና አስተሳሰብ ሽግግር የማምጣት ተፅዕኖ ሊኖረው ይችላል፡፡

    በአጠቃላይ ምርጥ ተሞክሮ ከማስፋታችን በፊት ብዙ ተጠቃሚዎችና ባለድርሻ አካላት የረኩበትና ማረጋገጫ የሰጡት መሆኑ፣ የምርጥ ልምዱ ባለቤቶች ምርጥ መሆኑን ያመኑበት፣ የተገኘበት ተቋም ከሌላ ወይም ተመሳሳይ ተቋማት ጋር ሲወዳደር በተጨባጭ ብልጫ ያሳየ መሆኑ እና ምርጥ ልምዱ ዘመኑ ከወለደው ቴክኖሎጅ ጋር አጣጥሞ መጠቀም የሚቻል መሆኑን ማጤን ይገባል።

    ምርጥ ተሞክሮ መለያ (መምረጫ) መስፈርት

    ምርጥ ተሞክሮ በመለየት ሥራ ላይ ለማዋል የሚያስችል ውጤታማ እና የተቀናጀ የአሰራር ስልት በመዘርጋት ተግባራዊ በማድረግ ነው፡፡ የመለየት ሥራዉ ሲሰራ ምርጥ ተሞክሮ ነው ወይስ አይደለም በሚል ግምገማ እና ምክንያታዊ ውሳኔ በመስጠት ይሆናል፡፡ በመሆኑም ከተለያዩ መረጃዎች መረዳት እንዲሚቻለው ምርጥ ተሞክሮ በቅድሚያ ምርጥ ስለመሆኑ በግልጽ በተዘጋጁ መስፈርቶች በመፈተሽ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

    ከዚህ በታች በዝርዝር በተመለከቱት መስፈርቶች በመጠቀም ምርጥ ተሞክሮን መለየት (መምረጥ) ያስችላል፡፡
    ሀ) ውጤታማነትና ቀልጣፋነት (Effectiveness & Efficency)
    ውጤታማነት መሰረታዊ የመለያ መስፈርት ሲሆን ምርጥ ተሞክሮው ያስመዘገበው ውጤት በግልጽ የሚታይ እና የሚለካ መሆን ይኖርበታል፡፡ የሚጠበቁ የግብ ስኬቶች በትክክል ስለመፈጸማቸው፣ ግቦችን በማሳካት አሳታፊነት፣ ተጠቃሚነትንና ፍትሃዊነትን እንዲሁም የዜጎች እርካታን ያጎናጸፈና በሰው ሀይል ላይ ለውጥ መፍጠሩ (ተነሳሽነትና ግንባር ቀደም መሆን)፡፡ በተለይ ውጤታማነቱ ቀጣይና አስተማማኝነቱን በሚገባ ፈትሾ ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በምርጥ ልምድነት ሊወሰድ የቀረበው ተሞክሮ ውጤት አዋጪ በሆነ ሀብትና ጊዜ የተገኘ መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ከጥረት ተደራሽ ግቦች አንጻር ተለይተው የተቀመጡ ስታንዳርዶች በምን ያህል እየተሳኩ ስለመሆኑ፣ የበጀት አጠቃቀም፣ የሰው ሃይል ብዛትና ምርታማነት፣ የመሳሪያዎች አጠቃቀም እና የክንውን ዑደት በትክክል ሊፈተሸ ይገባል፡፡
    ለ) ጠቀሜታው (Importance)
    በምርጥ ተሞክሮነት የቀረበው ልምድ የሚኖረው ፋይዳና ጠቀሜታ በሚገባ ተለይቶ ሊታወቅና ግልጽ ሊሆን ይገባል፡፡ ከመንግስት ፖሊሲና ስትራቴጂ አቅጣጫ ጋር ያለው ቁርኝነትና ትስስር፣ ተጨማሪ ለውጥ ለማስመዝገብ ያለው ብቃት በትኩረት ሊጤን ይገባል፡፡
    ሐ) የመስፋፋት ዕደሉ እና ዘላቂነቱ
    በምርጥ ተሞክሮ የቀረበው ልምድ በቀላሉ ሊስፋፋ የሚችል እና ዘላቂ ሊሆን ይገባል፡፡ ልምዱን ባለን ቴክኖሎጂ በመጠቀም ለማስፋትና ለማስተላለፍ የሚቻል ስለመሆኑ፣ የተገኘው ልምድ ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ ሆኖ ለማስፋፋት እንቅፋት የማይፈጥር፣ የመንግስት ፖሊሲና እስትራቴጂን የማይቃረንና በተስማሚነቱ ሊተገበር የሚችል እንዲሁም ከአካባቢያዊ ሁኔታ ጋር በማጣጣም ለመተግበር ያለው ምቹነት በጥንቃቄ ሊታይ ይገባል፡፡
    መ) የህብረተሰቡ ተሳትፎ
    በምርጥ ተሞክሮነት የቀረበው ልምድ ህብረተሰቡ በሚገባ የሚያውቀውና ተሳትፎ ያደረገበት መሆኑን ማረጋገጥና በህብረተሰቡ ዘንድ የተመሰከረለት መሆኑን እንዲሁም በቀጣይ በቀላሉ በህብረተሰቡ ዘንድ ለማስረጽ አመቺነቱን ማየት ያስፈልጋል፡፡
    ሠ) ስነ-ምግባራዊ ተቀባይነቱ
    በምርጥ ተሞክሮነት የቀረበው ልምድ የህብረተሰቡን ባህል እና ነባራዊ መልካም ነገሮች የማይቃረን በኅብረተሰቡ ዘንድ ያለው ተቀባይነት አስተማማኝ መሆኑን ማረጋገጥ ይጠይቃል፡፡ ምርጥ ልምዱ የሙስናና ብልሹ አሰራርን የማይጋብዝ ስለመሆኑ ሊረጋገጥ ይገባል፡፡
    ረ) የባለድርሻ አካላት ትብብር
    በምርጥ ተሞክሮነት የቀረበው ልምድ የባለድርሻ አካላት ያለው ድጋፍና ተቀባይነት ሊጤን ይገባል፡፡
    ሸ) የአስፈጻሚ አካላት ትኩረት
    በምርጥ ተሞክሮ የቀረበው ልምድ ከአስፈጻሚ አካላት ተቀባይነትና ድጋፍ ማግኘቱን ማረጋገጥ ያስፈልጋል፡፡

    ምርጥ ተሞክሮ መቀመር

    የምርጥ ተሞክሮ አቀማመር ሂደት ምርጥ ተሞክሮ ከተለየ በኋላ ቀጣዩ ሥራ የሚሆነው ምርጥ ተሞክሮውን በዝርዝር የመቀመር ሥራ መስራት ነው፡፡ በዝርዝር የመቀመር ሥራ በሚሰራበት ወቅት የሚከተሉትን ቅደም ተከተል በመጠበቅ መከናወን ይኖርባቸዋል፡፡
    ሀ) ቼክሊስት ማዘጋጀት
    በተለየው ምርጥ ተሞክሮ መሰረት ዝርዝር የቅመራ ሥራ መስራት የሚያስችል ቼክሊስት ይዘጋጃል
    ለ) መረጃ መሰብሰብ
    በተዘጋጀው ቼክሊስት መሰረት ከተቋሙ የበላይ ኃላፊዎችና ባለሙያዎች እንዲሁም ተሞክሮ ካለው ተቋም፣ ቡድን ወይም ግለስብ ጋር ወይይት ማካሄድና ዝርዝር መረጃ መሰብሰብ
    ሐ) የተሰበሰበውን መረጃ በዝርዝር መቀመር /Mapping/
    በዚህ ደረጃ በዝርዝር የተገኘውን መረጃ መሰረት በማድረግ ተቋሙ/ግለሰቡ ከየት ተነስቶ ምን ደረጃ ላይ እንደደረሰ በዝርዝር የሚታይበት ይሆናል፡፡
    የቅመራው ዝርዝር ይዘት ምርጥ ተሞክሮ በሚቀመርበት ወቅት የሚከተሉትን ዋና ዋና ጉዳዮች መሰረት በማድረግ በዝርዝር ሊዘጋጅ ይገባል፡፡ የቅመራው ሂደት /Mapping/ በሚከተለው ቅደም ተከተል ሊቀመጥ ይገባል፡-
    1) የተቋሙ ዳራ
    2) ተቋሙ ከለውጡ በፊት የነበረበት ሁኔታ
    3) በተቋሙ ለውጥ ለማምጣት የነበረው አስተሳሰብ
    4) ውጤቶችና ስኬቶች
    5) ስኬቱ የተገኘበት ዝርዝር ሂደት
    6) ለመተግበር ያጋጠማቸው ማነቆዎችና የተፈቱበት አግባብ
    7) በሂደቱ ውስጥ የተሳተፉ አካላትና የተጫወቱት ሚና
    8) ተሞክሮው ይበልጥ ውጤታማ ማድረግ እንዲቻል ሊከናወን የሚገባቸው ተግባራት
    9) መስል ወይም ሌሎች ተቋማት ከዚህ ሂደት ሊማሩት የሚገባ ቁም ነገር
    10) መደምደሚያና ማጠቃለያ አስተያየት

    ምርጥ ተሞክሮን የማስፋት ስትራቴጂ እና አስፈላጊነት

    የማስፋት ስትራቴጂ ማለት በአንድ አካባቢ ተሞክረው ስኬታማነታቸው የተረጋገጠ አሰራሮችን በሌሎች አካባቢዎች የሚመለከታቸውን አካላት በማሳተፍ ዘላቂነት ያለዉ አዎንታዊ ለውጥ የመጣበትን ምርጥ ተሞክሮ ማዳረስ ማለት ነው፡፡ ማስፋት ስንል በሕብረተሰቡ ዘንድ አዎንታዊ ተጽእኖ የሚኖራቸውን የመንግሥት ፖሊሲዎችንና እስተራቴጀዎችን በመተግበር በኩል ከውጤታማ ተቋማት የተገኙ ምርጥ ልምዶችን በሁሉም አካባቢ ተፈጻሚነት እንዲኖራቸው እቅድና፤ ፕሮግራም በመንደፍ ሥራ ላይ እንዲውሉ ማድረግ ነው፡፡

    በአጠቃላይ በተቋም ምርጥ ተሞክሮን ማስፋት ሲባል ከቁጥርና ከቦታ ስፋት ባሻገር በለውጥ ትግበራ ሂደት ውስጥ በአንድ ተቋም የታዩ ስኬታማና ሞዴል ተግባሮችን በመቀመር ከሌሎች ተቋማት ነባራዊ ሁኔታዎች ጋር በማስማማት ተግባራዊ ማድረግ ነው፡፡ የማስፋት ስትራቴጂ ጠቀሜታ በለውጥ ሂደት የተገኙ ምርጥ ተሞክሮዎች በሁሉም ተቋማት ተፈፃሚ እንዲሆኑና ወደ ላቀ ደረጃ በማሳደግ በቀጣይነት ብቃት ያለው እና ውጤታማ አፈጻጸም በማስመዝገብ የተቀመጡትን የልማትና የመልካም አስተዳደር ግቦች በማሳካት የዜጎችን ሁለንተናዊ ፍላጎት ለማሟላት ነው፡፡

    በመሰረታዊነት ምርጥ ተሞክሮ ማስፋት አስፈላጊነት እንደሚከተለው ተመላክቷል፡፡
    1 በአጭር ጊዜ በሁሉም አካባቢ ከፍተኛ የለውጥ እንቅስቃሴን ለመፍጠር፣
    2 በአንድ አካባቢ ውጤታማ የሆነን ተሞክሮ ያለ ተጨማሪ ወጪ ወደ ላቀ ደረጃ ለማስፋፋት
    3 ተቋማት በተሻለ አሰራር ዘላቂነት ባለው መንገድ ከተሞክሮው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ለማስቻል ናቸው፡፡

    ምርጥ ተሞክሮን እንዴት ማስፋት ይቻላል

    የምርጥ ተሞክሮ ቅመራ ሥራ ከተጠናቀቀ ቀጥሎ የሚኖረው ወሳኝ ጉዳይ ምርጥ ተሞክሮን ወቅታዊነቱን በመጠበቅ / Timeliness / የማስፋት ሥራ መስራት ነው፡፡ ምርጥ ተሞክሮ ተቀምሮ ማስፋት ካልተቻለ ውጤታማ ሊሆን አይቻልም፤ ለመለየትና ለመቀመር የተደረገው ጥረትና ድካም ውጤት አልባ ሆኖ ይቀራል፡፡ በመሆኑም ምርጥ ተሞክሮዎችን ለማስፋት ትኩረት ሊሰጠው የሚገባ ጉዳይ ስለሚሰፋው ምርጥ ተሞክሮ ማወቅ ተገቢ ይሆናል፡፡ በተጨማሪም የተቀመረውን ምርጥ ልምድ ለማስፋት አቅም መፍጠር ያስፈልጋል፡፡ አቅም የምንፈጥርበት መንገድ ደግሞ በአመለካከት፤ በክህሎት፣ በግብአት እና በድጋፍና ክትትል ያሉትን ችግሮች በትክክል በመለየት ተገቢ የመፍትኤ አቅጣጫ በመስጠት ተግባራዊ ይደረጋል፡፡

    ከዚህ አኳያ የማስፋት ስራ ልዩ ባሕርይ የተለያዩ ድርጅቶችና አካላት በመካከላቸው ትስስር በመፍጠር በተባበረ አቅም በአጭር ጊዜ በርካታ ሥራ መስራት የሚያስችል እንቅስቃሴ ማድረግን የሚያካትት ይሆናል፡፡
    የማስፋት ሥራ ለመስራት የሚከተሉትን ተግባራት በቅደም ተከተል መፈጸም ይገባል
    1. ተጠቃሚዎችን መለየት
    2. ከተጠቃሚዎች ጋር መወያየት፣አቅም መፍጠርና መግባባት ላይ መድረስ
    3. በስምምነቱ መሰረት ምርጥ ልምዱን ከራስ ተጨባጭ ሁኔታ ጋር ማላመድ
    4. ምርጥ ተሞክሮውን መተግበር
    5. አፈጻጸሙን ክትትል፣ ድጋፍና ግምገማ ማድረግ

    ምርጥ ተሞክሮ ማስፋትና ጥንቃቄው

    የማስፋት ሥራ ተለይቶ በተቀመረው ተሞክሮ መሰረት በሚከናወኑ ተግባራት ዙሪያ የታዩ አዳዲስ ግኝቶችን በመውሰድና በማዳበር የሚከናወን ይሆናል፡፡ ይሁን እንጂ ተግባራዊ በሚደረግበት ወቅት ትኩረት የሚሹና በጥንቃቄ መከናውን የሚገባቸውን ጉዳዮች በመለየት ተግባራዊ ማድረግ ይኖርብናል፡፡

    ምርጥ ተሞክሮ ከማስፋት በፊት ሊደረግ የሚገባ ጥንቃቄ እና ትኩረት የሚደረግባቸው ጉዳዮች

  • የምርጥ ተሞክሮ ተጠቃሚ በትክክል መለየቱን
  • የምርጥ ልምዱ ባለቤቶች ምርጥ መሆኑን ያመኑበት መሆኑ
  • የተጠቃሚዎች ፍቃደኝነትና ምርጥ ተሞክሮውን ከራሳቸው ተጨባጭ ሁኔታ ለመተግበር ያላቸውን ዝንባሌ ማረጋገጥና ስምምነት ላይ መድረሱን
  • ልምዱ የተገኘበት ተቋም ከሌላው ወይም መስል ተቋማት ጋር ሲወዳደር በተጨባጭ ብልጫ ያገኘ መሆኑ
  • ምርጥ ልምዱን ባለን ቴክኖሎጂ አጣጥሞ መጠቀም የሚቻል መሆኑ
  • ተያያዥ መረጃዎች
    © 2023 Lideta Subcity Job Creation. Designed by Markos Mulat G