መግቢያ

የጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ልማት የኢንዱስትሪ ልማት ስትራቴጂና የከተማ ልማት ፖሊሲ ላይ ተመስርቶ የራሱ ፕሮግራምና ዝርዝር የድጋፍ ፓኬጅ ተዘጋጅቶለት ላለፉት አመታት በኢንተርፕራይዞች ልማት አበረታች ውጤት አስገኝቷል፡፡ የድጋፍ ፓኬጁም በተመረጡ ዕድገት ተኮር ዘርፎች ላይ በማተኮር ለኢንተርፕራይዞች ድጋፍ መስጠት አስችሏል፡፡ በዚህም መሠረት በተለያዩ የምርትና የአገልግሎት ሙያዎች ለተሠማሩ በርካታ ኢንተርፕራይዞች አስፈላጊው የማደራጀት፤ የማሰልጠን፣ የፋይናንስና እንዲሁም የማምረቻና የመሸጫ ቦታ አቅርቦቶች እና የገበያ ትስስር ድጋፎች እንዲያገኙ በማድረግ ሰፊ የስራ ዕድል እንዲፈጠርና ለድህነት ቅነሳ ፕሮግራሙ የራሱን አስተዋጽኦ አበርክቷል፡፡

በከተማችን በአለፉት ዓመታት ለዜጎች የስራ ዕድል በመፍጠር እንዲሁም ኢንተርፕራይዞች የሚቋቋሙበትንና የሚደገፉበትን ፖሊሲና ስትራቴጂ በማውጣት በተግባር ላይ እንዲውል በማድረግ በከተማችን የሚታየውን የድህነትና የስራ አጥነት ችግሮችን በዘላቂነት በመቅረፍ የከተማዋን ኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ እሴቶች በማሳደግ በዘርፉ ልማት በርካታ አበረታች ውጤቶችን ማስመዝገብ ተችሏል፡፡ይህንንም ግብ የበለጠ ለማሳካት የሚያስችሉ የተለያዩ አሰራሮችንና የድጋፍ ማዕቀፍ ቀርፆ ለጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዞች ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

በዚሁ መሰረት ኢንተርፕራይዞች የሚቋቋሙበትንና የሚደገፉበት ማዕቀፎች እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ትርጓሜ

  1. ጥቃቅን ኢንተርፕራይዝ ማለት የኢንተርፕራይዙን ባለቤት፤ የቤተሰብ አባላትና ተቀጣሪ ሰራተኞች ጨምሮ እስከ አምስት ሰዎች ቀጥሮ የሚያሰማራና የጠቅላላ ካፒታሉ መጠን ህንፃን ሳይጨምር በአገልግሎት ዘርፍ ከብር 50000 (ሃምሳ ሺ) ወይም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከብር 100000 (አንድ መቶ ሺ) ያልበለጠ ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡
  2. አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ማለት የኢንተርፕራይዙን ባለቤት፤ የቤተሰብ አባላትና ተቀጣሪ ሰራተኞችን ጨምሮ ከስድስት እስከ ሰላሳ ሰዎች የሚያሰማራና የጠቅላላ ካፒታሉ መጠን ህንፃን ሳይጨምር በአገልግሎት ዘርፍ ከብር 50001 (ሃምሳ ሺህ አንድ) እስከ 500000 (አምስት መቶ ሺህ) ወይም በኢንዱስትሪ ዘርፍ ከብር 100001 (አንድ መቶ ሺህ አንድ) እስከ 1500000 (አንድ ሚልዮን አምስት መቶ ሺ) ያልበለጠ ኢንተርፕራይዝ ነው፡፡
  3. አደረጃጀት ማለት ዕውቀቱን፣ ሃብቱን፣ ጊዜውንና ጉልበቱን በማቀናጀት በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ ድጋፍ ለማግኘት የሚደራጁበት ነው፡፡
  4. “ኢንተርፕራይዝ” ማለት በጥቃቅንና አነስተኛ ዘርፍ የተደራጀ ህጋዊ ሰውነት ያለው ተቋም ነው፡፡
  5. “አንቀሳቃሽ” ማለት በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው በማምረት፤ ምርትን በመሸጥ ወይም አገልግሎት በመስጠት ስራ ላይ የተሰማራ የኢንተርፕራይዙ አባል ነው፡፡
  6. “ስራ ፈላጊዎች" ማለት ዕድሜያቸው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ የሆናቸውየመስራት ፍላጐት አቅምና ችሎታ ያላቸው የራሳቸውን ስራ በመፍጠርም ሆነ በመቀጠር ቋሚ ስራ የሌላቸው ነዋሪዎች ናቸው፡፡
  7. "የዩኒቨርሲቲና የኮሌጅ ምሩቃን ስራ ፈላጊዎች" ማለት ከመንግስትና ከግል ዩኒቨርሲቲዎች በዲግሪና ከዚያ በላይ፣ ከመንግስትና ከግል ኮሌጆች፣ የቴክኒክና ሙያ ትምህርትና ስልጠና ተቋማት ከደረጃ ከአንድ እስከ አራት የተመረቁና የመስራት ፍላጎትና ችሎታ እያላቸው የራሳቸውን ስራ በመፍጠርም ሆነ በመቀጠር ቋሚ የስራ መስክ የሌላቸው የከተማው ነዋሪ ነው፡፡
  8. "ፕሮጀክት ጥናት” ማለት በተለያዩ መንግስታዊና መንግስታዊ ባልሆኑ ተቋማት ያሉ የስራ ዕድሎችን በመለየት ስራ ፈላጊዎች ተጠቃሚ የሚሆኑበት የጥናት ሰነድ ነው፡፡
  9. “የንግድ ስራ ዕቅድ” ማለት የንግዱን ዓላማና ግብ በሚገባ የሚያብራራ ሲሆን ወደ ስራ ለመግባትና በተገቢው መንገድ ለማምረት፣ምርትና አገልግሎት ለመቆጣጠር የሚረዳ ሰነድ ነው፡፡
  10. “የሥራ ዕድል ፈጠራ” ማለት የመስራት አቅም እያላቸው በተለያየ ምክንያት ወደ ስራ ያልገቡ ዜጎችን በጊዜያዊ ወይም በቋሚ የስራ ዘርፎች ማሠማራት ነው፡፡
  11. “ቋሚ የሥራ ዕድል” ማለት የራሳቸውን ኢንተርፕራይዝ ፈጥረው የሚሰሩ ወይም በሌሎች ድርጅቶች ውስጥ ከአንድ ዓመት ያላነሰ ጊዜ በቋሚነት ተቀጥረው በፔይሮል ክፍያ በማግኘት የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው ነው፡፡
  12. “ጊዜያዊ የስራ ዕድል የተፈጠረላቸው” ማለት ለተወሰነ ስራ ከአንድ ወር ያነሰ ከአንድ አመት ያልበለጠ ጊዜ በራሳቸው ወይም በቅጥር የሚሰሩ ወይም በፔይሮል ክፍያ የስራ ዕድል የተፈጠረለት ነው፡፡
  13. “ነባር ኢንተርፕራይዝ” " ማለት የአንድ ኢንተርፕራይዝ ጠቅላላ ሀብት ሲቀነስ ዕዳ ማለት ነው፡፡
  14. “አዲስ ኢንተርፕራይዝ” ማለት በኢንተርፕራይዞች አደረጃጀት መሠረት ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው ወደ ስራ ከተሰማሩ አንድ ዓመት ያልሞላቸው ሲሆኑ ከተቋሙ የድጋፍ አገልግሎት ያገኙ ወይም ያላገኘ ነው፡፡
  15. “የግል ኢንተርፕራይዝ” ማለት በኢንተርፕራይዞች አደረጃጀት መሠረት ሕጋዊ ፈቃድ አግኝተው ወደ ስራ ከተሰማሩ አንድ ዓመት ያልሞላቸው ሲሆኑ ከተቋሙ የድጋፍ አገልግሎት ያገኙ ወይም ያላገኘ ነው፡፡
  16. “ህብረት ሽርክና ማህበር” ማለት ህጋዊ ሰውነት ያለው ከንግዱ ማህበራት ሁሉ ቀላል ቅርጽ ያለው፣ የሸሪኮች አነስተኛ ቁጥር ሁለት ሰው ሲሆን ትልቁ መስራቾች ቁጥር ገደብ የሌለው አና የአነስተኛ የመነሻ ካፒታሉ በውስጠ ደንቡ ውስጥ አባላቱ ዕጣ /ሼር/ ድምር በመነሻ ካፒታልነት በመያዝ የሚመሰረት የንግድ ማህበር አይነት ነው፡፡
  17. “ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር” ማለት ከሁለት አባላት ያላነሰ ከሃምሳ አባላት ያልበለጠ የሚቋቋም ሆኖ የማህበሩ መነሻ ካፒታል ከብር 15000.00 /አስራ አምስት ሺ/ ያላነሰ፣ የማህበሩ አክሲዮን እኩል በሆነ የአክሲዮን ዋጋ የተከፋፈለ ሆኖ የአንድ አክሲዮን ዋጋ ከብር 10 /አስር/ ያላነሰ ሲሆን አባላቱም የተወሰነ ኃላፊነት ያለው ድርጅት ወይም ማህበር ነው፡፡
  18. “አክሲዮን ማህበር” ማለት የማህበሩ አበላት አምስትና ከዚያ በላይ የሚቋቋም ሆኖ የማህበሩ መነሻ ካፒታል ከብር 50000.00 /ሃምሳ ሺ /ያላነሰ፣ የማህበሩ አክሲዮን እኩል በሆነ የአክሲዮን ዋጋ የተከፋፈለ ሆኖ የአንድ አክሲዮን ዋጋ ከብር 10 /አስር/ ያላነሰ ሲሆን አባላቱም የተወሰነ ኃላፊነት ያለው ድርጅት ወይም ማህበር ነው፡፡፡፡
  19. የኢንተርፕራይዝ አደረጃጀት መርሆዎች

    የኢንተርፕራይዝ አደረጃጀት የሚከተሉት መርሆዎች ይኖሩታል፤
    1. የስራ ዕድል ፈጠራው በስራ ፈላጊነት ለተለዩና ለተመዘገቡ ነዋሪዎች ብቻ ነው፤
    2. የወጣቶች የሴቶች እና የአካል ጉዳተኞችን ተሳትፎና ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ፤
    3. የስራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ አማራጮችን አሟጦ መጠቀም፤
    4. ለስራ ፈላጊዎች ሁሉን አቀፍ ድጋፍ በመስጠት የስራ ዕድል እንዲፈጠርላቸው ማድረግ፤
    5. የሚሰጡ ህጋዊነት የማስፈንና መንግስታዊ ድጋፎች በአንድ ማዕከል አገልግሎቶች መስጫ ጣቢያ እንዲያልቁ ማድረግ፤
    6. ቀልጣፋና ፍትሃዊ የሆነ አገልግሎት መስጠት፤
    7. የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችንና ባለድርሻ አካላትን አሳትፎ መስራት፡፡

    በጥቃቅንና አነስተኛ ለመደራጀት የተፈቀዱ የዕድገት ተኮር የስራ ዘርፎች፡-

    1. ማኑፋክቸሪን ስራ ዘርፍ፣
    2. ኮንስትራክሽን ስራ ዘርፍ፣
    3. ከተማ ግብርና ስራ ዘርፍ፣
    4. አገልግሎት ስራ ዘርፍ፣
    5. ንግድ ስራ ዘርፍ፣

    የአደረጃጀት ዝርዝር ዘርፎችና ንዑስ ዘርፎች ለማወቅ ከፈለጉ ይህን የአደረጃጀት ዘርፎች ይጫኑ

    የስራ ፈላጊዎች ግንዛቤ ፈጠራ፤ ምዝገባ እና ስልጠና

    የስራ ፈላጊዎች ግንዛቤ ፈጠራ

    1. ከባለድርሻ አካላት ጋር በመሆን በንቅናቄ ለስራ ፈላጊዎችና ለተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ስለ ጥቃቅንና አነስተኛ ፖሊሲና ስትራቴጂ በተለያዩ መድረኮችና ሚዲያዎች የግንዛቤ ፈጠራ ስራ መሰራት አለበት፡፡
    2. ለስራ ፈላጊዎች የጥቃቅንና አነስተኛ የድጋፍ ማዕቀፎች ላይ በቂ ግንዛቤ እንዲይዙ መደረግ አለበት፡፡
    3. የግንዛቤ ፈጠራ ስራው በዋናነት ወጣቶች እና ሴቶች የዩኒቨርስቲ እና የኮሌጅ ሙሩቃን አካል ጉዳተኖች ስደት ተመላሾች ኤች አይቪ ተጋላጭ ለሆኑ የህብረተሰብ ክፍሎች ላይ ትኩረት ማድረግ አለበት፡፡

    የስራ ፈላጊዎች ልየታና ምዝገባ

    በስራ ፈላጊነት ልየታ ለመመዝገብ መሟላት ያለባቸው መስፈርቶች፡-

    ሀ. የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ ያለው መሆን አለበት፤
    ለ. ዕድሜው ከ18 ዓመት በላይ የሆነ መሆን አለበት፤
    ሐ. በግሉ ቋሚ ስራ የሌለው ወይም በቋሚ ቅጥር ተቀጥሮ የማይሰራ መሆን አለበት፤
    መ. ከህዝብ አደረጃጀት ምንም አይነት ስራ እንደሌለው የሚገልጽ ማስረጃ መቅረብ አለበት፤
    ሠ. የዩኒቨርሲቲና የቴክኒክና ሙያ ምሩቃን ከሆኑ በስራ ፈላጊነት ለመመዝገብ ሲመጡ የተመረቁበትን ዋናውና ኮፒ የትምህርት ማስረጃ ይዘው መቅረብ አለበት፡፡

የስራ ፈላጊዎች ስልጠና፡-

  1. እንደ ስልጠናው ዓይነትና የቆይታ ጊዜ በመለየት ስራ ፈላጊዎች በመረጡት የስራ ዘርፍ በቴክኒክና ሙያ እንዲሰለጥኑ በማስገባት ስልጠናውን እስኪጨርሱ ድረስ ተገቢው ክትትል መደረግ አለበት፡፡
  2. ሰልጣኞች ስልጠናቸውን ሲያጠናቅቁ የሙያ ብቃት ምዘና ተመዝነው ብቁ ሆነው የወጡ ሰልጣኖችን መረጃ በዘርፍ መያዝ አለበት፡፡
  3. የክፍለ ከተማ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት በቴክኒክና ሙያ ስልጠናቸውን አጠናቅቀው በኢንተርፕራይዝ ለመደራጀት ብቁ የሆኑትን ስራ ፈላጊዎችን ዝርዝር መረጃ አረጋግጦ መቀበል አለበት፡፡
  4. በተለያዩ ምክንያት በቴክኒክና ሙያ ስልጠናቸውን ያላጠናቀቁ ሰልጣኞች መረጃ በአግባቡ አደራጅቶ መያዝ አለበት፡፡
  5. በቴክኒክና ሙያ ስልጠና ተቋማት ስልጠና የማይሰጥባቸው የስራ ዘርፎች ሲያጋጥሙ ከሌሎች አካላት ጋር በመተባባር ስልጠና እንዲያገኙ መደረግ አለበት፡፡

በጥቃቅንና አነስተኛ ለመደራጀት የሚያስፈልጉ ቅድመ ሁኔታዎች፡-

  1. ዕድሜው 18 ዓመት እና ከዚያ በላይ መሆን አለበት፡፡
  2. የአዲስ አበባ ከተማ የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ ያለው መሆን አለበት፡፡
  3. የስራ ፈላጊ ካርድ ማቅረብ የሚችል መሆን አለበት፡፡
  4. ከሚኖርበት ወረዳ ወደ ሌላ ወረዳ ሄዶ ለመደራጀት ሲፈልግ ከሚኖርበት ወረዳ የስራ ዕድል ፈጠራና ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ያለመደራጀት ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡
  5. የኢንተርፕራዝ አደረጃጀት ዓይነቶች፡-

    1. በግል ኢንተርፕራይዝ፣
    2. በንግድ ህግ ማህበራት መሰረት፡-
    ሀ. ህብረት ሽርክና ማህበር፣
    ለ. ሃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር፣
    ሐ. አክሲዮን ማህበር፡፡

    በግል ኢንተርፕራይዝ ህጋዊ ሰውነት አግኝቶ ለመስራት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች፡-

    1. የአመልካቹን ማንነት በግልጽ የሚያሳይ በ6 ወራት ጊዜ ውስጥ የተነሳው አራት የፓስፖርት መጠን ያለው ፎቶ ግራፍ ማቅረብ አለበት፡፡
    2. የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ሰርተፍኬት ማቅረብ አለበት ፡፡
    3. የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ለሚያስፈልጋቸው የስራ ዘርፎች ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማቅረብ አለበት፡፡
    4. የንግድ የስራ አድራሻ የባለቤትነት ማረጋገጫ ወይም የጸደቀ የኪራይ ውል ወይም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት የኪራይ ውል ወይም ከአካባቢው መስተዳደር አካል የተሰጠ የጽሑፍ ማረጋገጫ ማቅረብ አለበት፡፡
    5. ለንግድ ስራው የመደበውን ካፒታል ማሳወቅ አለበት፡፡
    6. ለሚሰራው ስራ የንግድ ስራ ዕቅድ ማቅረብ አለበት፡፡
    7. በንግድ ህግ ማህበራትን ለማደራጀት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች፡-

      የኀብረት ሽርክና ማኀበር አደረጃጀት

      የኀብረት ሽርክና ማህበር አደረጃጀት ሕጋዊ ሕልውና ያለው ከንግድ ማኀበራት ወይም ድርጅቶች ሁሉ ቀላል ቅርጽ ያለው አደረጃጀት ነው፡፡ በህብረት ሽርክና አደረጃጀት የሸሪኮች አነስተኛ ቁጥር ሁለት ብቻ ሲሆን የአነስተኛ ካፒታል ጥያቄ ገደብ የለበትም፡፡ ካፒታሉ በውስጠ ደንቡ ውስጥ ቢካተትም ከምዝገባ በፊት መክፈሉ አስፈላጊ አይደለም፡፡ የሙያ ወይም የአገልግሎት መዋጮ የተፈቀደ ነው፡፡

      በህብረት ሽርክና ማህበር ለማደራጀት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች

      1. የስራ አጥ መታወቂያ ካርድ፣
      2. በሁሉም መስራች አባላት የተፈረመ ማመልከቻ ማቅረብ፣
      3. የአባላቱ የነዋሪነት መታወቂያ ካርድ ኮፒ ማቅረብ፣
      4. የፀደቀ የንግድ ስም ስያሜ ማስረጃ፣
      5. የንግድ ማህበሩን ስራ አስኪያጅ ማንነት በግልጽ የሚያሳይ ከስድስት ወራት በፊት የተነሳው አራት የፓስፖርት መጠን ያላቸው ፎቶ ግራፍ ማቅረብ አለበት፡፡
      6. የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡
      7. የንግድ የስራ አድራሻ የባለቤትነት ማረጋገጫ ወይም የፀደቀ የኪራይ ዉል ወይም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት የኪራይ ውል ወይም ከአካባቢው መስተዳደር አካል የተሰጠ የጽሑፍ ማረጋገጫ ማቅረብ አለበት፡፡
      8. የብቃት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት ለሚያስፈልጋቸው የስራ ዘርፎች ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማቅረብ አለበት ፡፡
      9. የአባላት ቁጥር ሁለት እና ከዚያ በላይ መሆን አለበት፡፡
      10. በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ የጸደቀ መመስረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ማቅረብ አለበት፡፡
      11. ለሚሰራው ስራ የንግድ ስራ ዕቅድ ማቅረብ አለበት፡፡
      12. በኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር ለመደራጀት የሚያስፈልጉ መስፈርቶች፡-

        1. የንግድ ማህበሩ ስራ አስኪያጅ ማንነት በግልጽ የሚያሳይ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተነሳው አራት የፓስፖርት መጠን ያላቸው ፎቶ ግራፎች ማቅረብ አለበት፡፡
        2. የጸደቀ የንግድ ስም ስያሜ ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡
        3. የግብር ከፋይነት መለያ ቁጥር ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡
        4. የንግድ የስራ አድራሻ የባለቤትነት ማረጋገጫ ወይም የጸደቀ የኪራይ ውል ወይም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት የኪራይ ውል ወይም ከአካባቢው መስተዳደር አካል የተሰጠ የጽሑፍ ማረጋገጫ ማቅረብ አለበት፡፡
        5. የብቃት ማረጋገጫ ለሚያስፈልጋቸው የስራ ዘርፎች ብቃት ማረጋገጫ ሰርተፊኬት ማቅረብ አለበት ፡፡
        6. የአባላት ቁጥር ሁለት እና ከዚያ በላይ መሆን አለበት፡፡
        7. በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ የጸደቀ መመስረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ማቅረብ አለበት፡፡
        7. የአባላት ቁጥር ከ2 እስከ 50 መሆን አለበት፡፡
        8. ለሚሰራው ስራ የንግድ ስራ ዕቅድ ማቅረብ አለበት፡፡

        በአክሲዮን ማህበር ለመደራጀት፡-

        1. የስራ አስኪያጁ የታደሰ የነዋሪነት መታወቂያ ዋናውና አስፈላጊ ገፆች ፎቶ ኮፒ ማቅረብ አለበት፡፡
        2. የአክሲዮን ማህበሩ ስራ አስኪያጅ ማንነት በግልጽ የሚያሳይ በስድስት ወራት ጊዜ ውስጥ የተነሳው አራት የፓስፖርት መጠን ያላቸው ፎቶ ግራፎች ማቅረብ አለበት፡፡
        3. የማህበሩ አባላት ቁጥር 5 እና ከዚያ በላይ መሆን አለበት፡፡
        4. ከተፈረመ የአክሲዮን ሽያጭ ቢያንስ አንድ አራተኛ ገንዘብ ተክፍሎ በዝግ ሂሳብ መቀመጡ ከባንክ ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡
        5. ያንዱ አክሲዮን ዋጋ ከ10 ብር ያነሰ መሆን የለበትም፡፡
        6. የንግድ የስራ አድራሻ የባለቤትነት ማረጋገጫ ወይም የጸደቀ የኪራይ ውል ወይም መንግስታዊና መንግስታዊ ካልሆነ ድርጅት የኪራይ ውል ወይም ከአካባቢዉ መስተዳደር አካል የተሰጠ የጽሑፍ ማረጋገጫ ማቅረብ አለበት፡፡
        7. የአክሲዮን ድርሻ ሰርተፊኬት ናሙናና የውስጥ መተዳደሪያ ደንብ ለመዝጋቢው አካል ማቅረብ አለበት፡፡
        8.ለሚሰራው ስራ የንግድ ስራ ዕቅድ ማቅረብ አለበት፡፡

        የህጋዊ ሰውነት ሰርተፍኬት አሰጣጥ

        በግልም ሆነ በማህበር በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ወደ ስራ ለሚገቡ ኢንተርፕራይዞች ለመደራጀት የሚያስፈልጉ ተብለው የተዘረዘሩትን መስፈርቶች አሟልተው የመመስረቻ ጽሁፍና መተዳደሪያ ደንባቸውን ካፀደቁ በጥቃቅንና አነስተኛ የተደራጁ መሆናቸውን የሚገልጽ የህጋዊነት ማረጋገጫ ሰርተፍኬት በአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ጣቢያ ተዘጋጅቶ እንዲሰጣቸው ይደረጋል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ ተደራጅተው ወደ ስራ የሚገቡ ስራ ፈላጊዎች አደረጃጀታቸውን እንደጨረሱ በጀማሪ ደረጃ የሚሰጣቸው ሰርተፍኬት ይሰጣቸዋል፡፡ በጥቃቅንና አነስተኛ መደራጀታቸውን የሚገልጽ ሰርተፍኬት ከተሰጣቸው በኋላ የንግድ ምዝገባና ፈቃድ እንዲያወጡ ይደረጋል፡፡

        በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ማህበራት ውስጥ የተጓደሉ አባላት ስለማሟላት፡-

        1. ኢንተርፕራይዙ የማህበር አባላት ሲጓደልበት እና የተጓደሉ አባላትን ለማሟላት ሲፈልግ በቅድሚያ ተደራጅቶ ለሚሰራበት ወረዳ የለቀቀውን አባልና አዲስ የሚተካውን አባል ማንነት በጽሁፍ ማሳወቅ አለበት፡፡
        2. በተጓደለው አባላት የሚተኩ ስራ ፈላጊዎች ለመደራጀት የተቀመጡ መስፈርቶችን ያሟላ መሆን አለበት፡፡
        3. በመመስረቻ ጽሑፍና በመተዳደሪያ ደንቡ መሰረት ማህበሩ በህጋዊ ኦዲተር የተረጋገጠ ሂሳብ ካሰራ በኋላ ባለው የካፒታል ድርሻ መሰረት መክፈል የሚችል መሆን አለበት፡፡
        4. አባላት የተጓደለበት ማህበር ከገቢዎች ጽ/ቤት መልቀቂያ ወይም ክሊራንስ ማቅረብ አለበት፡፡
        5. በተጓደለው ማህበር የሚሟሉትን አባላት በቃለ ጉባኤ ተደግፎ በሰነዶች ማረጋገጫ መጽደቅ አለበት፡፡
        6. ኢንተርፕራይዞች የተጓደሉ አባላትን ለማሟላት ወደ ሰነዶች ማረጋገጫ ጽ/ቤት ሲሄዱ ተደራጅተው ከሚሰሩበት የወረዳ ጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ ልማት ጽ/ቤት ስለሚተካው ሰው ትክክለኛ ስራ ፈላጊነት ማረጋገጫ የድጋፍ ደብዳቤ ይዞ መሄድ አለበት፡፡

        አንተርፕራይዝ ህጋዊ ሰውነት ከተሰጠዉ በኋላ የሚፈርስባቸው ምክንያቶች፡-

        1. በፍርድ ቤት ውሳኔ እንዲፈርስ ሲወሰን፣
        2. የኢንተርፕራይዙ መስራች አባላት ሦስት አራተኛው ማህበሩ እንዲፈርስ ሲስማሙወይም ሲወስኑ፣
        3. ከንግድ ህጉ ዓላማ ውጪ ተሰማርቶ የተገኘ ሲሆን፤
        4. ኃላፊነቱ የተወሰነ የግል ማህበር እና በህብረት ሽርክና ማህበር የአባላት ብዛት ከ2 በታች ሲሆን፤
        5. በአክሲዬን የተደራጁ ከሆነ የአባላት ቁጥር ከ 5 በታች ሲሆን፡፡

        የስም ለውጥ ለሚያደርጉ ኢንተርፕራይዞች መደረግ ያለበት ድጋፍ፡-

        1. ኢንተርፕራይዙ የስም ለውጥ ከማድረጉ በፊት ከማንኛውም ዕዳ ነፃ መሆኑን በማስረጃ ማረጋገጥ አለበት፡፡
        2. ኢንተርፕራይዙ የስም ለውጥ ማድረጉን የንግድ ስያሜውን በሰጠው አካል አረጋግጦ ለሚመለከተው ሁሉ ማሳወቅ አለበት፡፡
        3. ኢንተርፕራይዙ የስም ለውጥ ማድረጉን አረጋግጦ መረጃው ወቅታዊ መደረግ አለበት፡፡
        4. በህብረት ሽርክና የተደራጁ ኢንተርፕራይዞች የኢንተርፕራይዙ ስያሜ ላይ ስሙ የተጠቀሰ አባል የሚለቅ ከሆነ የማህበሩ ስም መቀየር አለበት፡፡

        የአድራሻ ለውጥ ሲደረግ የሚሰጡ አገልግሎቶች፡-

        1. ማህበሩ ቀደም ብሎ ሲሰራ ከነበረበት የመስሪያ ቦታ በተለያዩ ምክንያት አድራሻ ለውጥ ሲያደርግ አድራሻ የቀየረበትን ህጋዊ መረጃ በማጣራት ፋይሉን ኮፒ በማስቀረት ዋናውን ወደ ቀየረበት የስራ አድራሻ መላክ አለበት፡፡
        2. የኢንተርፕራይዙ አድራሻ ለውጥ ማድረጉን አረጋግጦ ለሚመለከተው ሁሉ ማሳወቅ አለበት፡፡

        በጥቃቅንና አነስተኛ ኢንተርፕራይዝ የተደራጁ ማህበራት የዘርፍ ለውጥ ሲያደርጉ መሟላት ያለባቸው መረጃዎች፡-

        1. በስራ አስኪያጁ የቀረበ ማመልከቻ በመመስረቻ ጽሑፍ እና በመተዳደሪያ ደንቡ መስረት በጠቅላላ ጉባኤው የጸደቀ ቃለ ጉባኤ መቅረብ አለበት፡፡
        2. ለውጥ የሚያደርጉበት የስራ ዘርፍ የብቃት ማረጋገጫ የሚያስፈልገው ከሆነ የብቃት ማረጋገጫ ስርተፍኬት መቅረብ አለበት፡፡
        3. ከገቢዎች ጽ/ቤት ቀድሞ ተሰማርቶ የነበረበትን የስራ ዘርፍ መልቀቂያ ወይም ክሊራንስ ማቅረብ አለበት፡፡
        4. ቀድሞ የነበረውን ንግድ ፍቃድ ይዞ መቅረብ አለበት፡፡
        5. በሰነዶች ምዝገባና ማረጋገጫ የጸደቀ መመስረቻ ጽሑፍና መተዳደሪያ ደንብ ማቅረብ አለበት፡፡
        6. የዘርፍ ለውጥ ስልጠናና የብቃት ማረጋገጫ የሚፈልግ ዘርፍ ከሆነ ማቅረብ መቻል አለበት፡፡
        7. የመስሪያ ቦታው የመንግስት ከሆነ የመስሪያ ቦታው የዘርፍ ለውጥ የተደረገበትን ማስረጃ ማቅረብ አለበት፡፡

ተያያዥ መረጃዎች
© 2023 Lideta Subcity L/E/I/D/Office. Designed by Markos Mulat G