በልደታ ክ/ከተማ"ኢትዮጲያ ታምርት" በሚል መሪ ቃል የአምራች ኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም ለማሳደግ የሚያስችል ምክክር ተካሄደ።

በምክክር ፕሮግራሙ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት የክ/ከተማው ምክትል ስራ አስፈፃሚ እና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ኤኬታ እንደተናገሩት የኢትዮጲያ ታምርት ንቅናቄው ዋና ዓላማ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ማነቆዎችን ለመፍታት፣ ለዘርፉ ዘላቂ ልማትና ተወዳዳሪነት ምቹ ሁኔታዎች ለመፍጠር፣ ስትራቴጅክ ምርቶችን አመርቶ መተካትና የውጭ ምንዛሬ አቅምን ለማሳደግ ፣የዘርፉን ምርትና ምርታማነት በማሳደግ የስራ እድል ፈጠራ አቅምን ለማሻሻል እና ዘርፉ ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር የበኩሉን አስተዋፆ እንዲወጣ ለማስቻል ነው ብለዋል።

አቶ ብርሀኑ አክለውም እንደ ክፍለ ከተማችን ንቅናቄው ከተጀመረ በኃላ 504 ችግሮችን በመለየት ባለፍት 6 ወራት 270 የሚሆኑትን ችግሮች ፈተናል ያሉ ሲሆን የተፈቱ ችግሮችም የቦታ አቅርቦት፣የብድር አቅርቦት፣የአቅም ግንባታ ስልጠናዎች፣ ምርቶቻቸውን የማስተዋወቅ እድል መፍጠር እና የተለያዩ የመሰረተ ልማት ማነቆዎችን የመፍታት ስራ መሆናቸውን ገልፀው እነዚህ ማነቆዎች ከሞላ ጎደል በመፈታታቸው ኢንዱስትሪዎቻችን ተኪ ምርት ከማምረት አልፈው ኤክስፖርት ስታንዳርድ ያለው ምርት እያመረቱ ይገኛሉ ብለዋል።

ኢንዱስትሪዎቻችን በኢኮኖሚው ላይ ትርጉም ያለው ለውጥ እና እድገት እንዲያስመዘግቡ በየደረጃው ያለ አመራርና ባለድርሻ አካላት ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል ያሉት አቶ ብርሀኑ ስራው በአጭር ጊዜ የሚጠናቀቅ ሳይሆን በጥረት ፣ በቁጭትና በእልህ መስራት የሚጠይቅ፣ ጤናማ የውድድር ስሜት መላበስን የሚፈልግ ፣ ሰርቸ መለወጥ እችላለሁ የሚል ውስጣዊ ጥንካሬን መላበስ የሚሻ በመሆኑ ተባብረንና ተደጋግፈን ዘርፉን ማሳደግ ይኖርብናል በማለት ተናግረዋል።

በቢሮ ኃላፊ ደረጃ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ኢዘድን ሙስብሀ በበኩላቸው በኢትዮጲያ ታምርት ንቅናቄ የአምራች ኢንዱስትሪዎችን ችግር በመቅረፍ ምርትና ምርታማነትን እንዲሻሻል ማድረግ ተችሏል ብለው ከፍተኛ አመራሩም ለተግባሩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራቱና ኢንዱስትሪዎችን በተለያየ መልኩ በመደገፍ ለውጥ ማምጣት ችለናል ሲሉ ገልፀዋል።

የኢንዱስትሪዎችን የማምረት አቅም በማሳደግ፣ የማምረቻ ወጭን በመቀነስ እና ተወዳዳሪነትን በማሳደግ ተወዳዳሪ ሁነን ወደ ዓለም አቀፍ ገበያ እንገባለን ያሉት ኃላፊው ኢንዱስትሪዎችን በመደገፍ ለቀጣይ አቅም እንዲፈጥሩና ለኢኮኖሚ ማሻሻያው አስተዋፆ እንዲያደርጉ ይሰራል ሲሉ ገልፀዋል።

ተያያዥ መረጃዎች
© 2023 Lideta Subcity Job Creation. Designed by Markos Mulat G