ምቹ የስራ አካባቢዎችን በመፍጠር ሴቶች ውጤታማ እንዲሆኑ መስራት ይገባል ሲል የልደታ ክፍለ ከተማ የስራ፣ኢንተርፕራይዝና ኢንደስትሪ ልማት ጽ/ቤት ገለፀ። ጽ/ቤቱ አለም አቀፍ የሴቶች ቀንን ምክንያት በማድረግ"ምቹ የስራ ሁኔታ ለሴት ሰራተኞች"በሚል መሪ ቃል የውይይት መድረክ አካሂዷል።

በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የስራ፣ ኢንተርፕራይዝ ኢንደስትሪ ልማት ቢሮ የአሰሪና ሰራተኛ ጉዳይ ዘርፍ የስልጠና ባለሙያ ወ/ሮ አበባ ገብሩ እንደገለጹት ሴቶች ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ችግሮቻቸውን ለመፍታት እንቅስቃሴዎችን በተደራጀ መንገድ በማከናወን የሴቶች ቀንን ከማክበር ባለፈ ተጠቃሚነታቸውን ማረጋገጥ የአለም አቀፍ የሴቶች ቀን ዓላማ መሆኑን ጠቁመው የሴቶች ሁለንተናዊ ተሳትፎ በማሳደግ በሀገራችን ዕድገት የበኩላቸውን ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል።

ወ/ሮ አበባ አክለውም ሴቶች በሚሰሩበት ቦታ ለተመሳሳይ ስራ ተመሳሳይ ክፍያን ተግባራዊ በማድረግ የሴቶች እኩልነትን ማረጋገጥ እንደሚገባ ገልጸው ሴቶች በስራ ቦታቸው ላይ ውጤታማ እንዲሆኑ የስራ ቦታ ደህንነታቸውን ማረጋገጥ ይገባል ብለዋል። በልደታ ክፍለ ከተማ አስተዳደር የስራ፣ኢንተርፕራይዝ ኢንደስትሪ ልማት ጽ/ቤት የስራ ስምሪትና ሴፍትኔት ዘርፍ አስተባባሪ አቶ ገብሬ አያሌው እንደተናገሩት ስራዎች ውጤታማ የሚሆኑት የሴቶች ተሳትፎ ማረጋገጥ ስንችል መሆኑን በመጥቀስ አለም አቀፍ የሴቶች ቀን ሲከበርም የሴቶችን በስራ ላይ ያላቸውን ተሳታፊነትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ ምቹ የስራ አካባቢዎችን በመፍጠር ሊሆን ይገባል ብለዋል።

ምንጭ ፡- የልደታ ክ/ከተማ ኮሙኑኬሽን ጽ/ቤት።
ተያያዥ መረጃዎች
© 2022 Lideta Subcity Job Creation. Designed by Markos Mulat G