የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ክብርት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ ባስተላለፍት መልዕክት ከወንዝ ዳርቻና በልማት ምክንያት ለተነሱ ዜጎች በግልፅኝነትና ፍትሀዊነት የሚገባቸውን የመኖሪያ ቤት፣ የመሬትና የካሳ ክፍያ ሰጥተናል ፥አዲስ አበባን ለነዋሪዎቿ ውብ፣ ምቹና አረንጓዴ ለማድረግ የጀመርነውን ጥረት የከተማችን ነዋሪዎች ማገዝ ይኖርባቸዋል ብለው ከተማችን ስትለማ ከማንም በላይ ተጠቃሚው ነዋሪዎቿ ናቸው ሲሉ ገልፀዋል።

ከንቲባዋ አክለውም ዛሬ የእድሉ ተጠቃሚ የሆኑ በወንዝ ዳርቻ ይኖሩ የነበሩ ዜጎች በተበከለ ፍሳሽ ምክንያት ለጤና ችግር ብሎም ክረምት በመጣ ቁጥር ለጎርፍ አደጋ ስጋት ተጋላጭ ነበሩ ያሉ ሲሆን እነሱን አንስተን ደረጃውን በጠበቀ ምቹ የመኖሪያ ቤት እንዲኖሩ ከማድረግ ባለፈ ወንዞችን በማከም፣ በማፅዳትና በማስዋብ የወንዝ ዳር መዝናኛዎችን እየገነባን የቱሪስት መስህብ እና የገቢ ምንጭ እንዲሆኑ እናደርጋለን ሲሉ ተናግረዋል።

የልደታ ክ/ከተማ ዋና ስራ አስፈፃሚ አቶ ሰይድ ዓሊ እንደተናገሩት የከተማችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና ለማረጋገጥ ዘርፈ ብዙ ስራዎች እየተከናወኑ ነው ፤ለአብነትም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ የሚኖሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ያደረጉ የ60/90 ቀናት ሰው ተኮር ፕሮጀክቶችን መጥቀስ ይቻላል ብለው በ60/90 ቀናት ፕሮጀክቶች የበርካታ ነዋሪዎችን ህይወት መቀየር ተችሏል ሲሉ ገልፀዋል።

በክፍለ ከተማችን ለመኖሪያ ምቹ ያልሆኑ መንደሮች፣ሰፈሮችና አካባቢዎች መኖራቸውን የገለፁት ዋና ስራ አስፈፃሚው ሰው ተኮር ስራዎቻችንን በማጠናከርና መንደሮችን መልሰን በመገንባት ውብና ለነዋሪዎቿ ምቹ የሆነች ልደታን እንፈጥራለን ብለዋል።

ዛሬ ለነዋሪዎቻችን ያስተላለፍነው የመኖሪያ ቤት በክብርት ከንቲባችን ወ/ሮ አዳነች አቤቤ የ24 ስዓት ክትትል እና ድጋፍ የተገነባ ነው ያሉት ስራ አስፈፃሚው ለከንቲባዋም ምስጋና አቅርበዋል።

የከተማ ውበትና አረንጓዴ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር ጀማል ጀምበር በበኩላቸው ዛሬ የመኖሪያ ቤት ተጠቃሚ የሆኑ ዜጎች በወንዝ ዳርቻ የሚኖሩ፤ በሽታ ምክንያት ለተለያዩ በሽታዎ ተጠቂ የነበሩና ለጎርፍ አደጋ ተጋላጭነት ከፍተኛ ስጋት የነበረባቸው ናቸው ብለው በቀጣይም የከተማ አስተዳደሩ ልዩ ድጋፍ በማድረግ ነዋሪዎቹን ከጎርፍ ስጋት ነፃ እያደረገ ወንዞችን ደግሞ እያለማ ይቀጥላል ሲሉ ተናግረዋል።

ምንጭ ፡- የልደታ ክ/ከተማ ኮሙኑኬሽን ጽ/ቤት።
ተያያዥ መረጃዎች
© 2023 Lideta Subcity Job Creation. Designed by Markos Mulat G