የልደታ ክፍለ ከተማ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽ/ቤት የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የግንባታ ፕሮጀክት የመሰረተ- ድንጋይ የተጣለበትን 12ኛ ዓመት ክብረ በዓል መነሻ በማድረግ የህዝብ ንቅናቄ እና የገቢ አሰባሰብ መርሀ ግብር አስጀምሯል።

የአዲስ አበባ ከተማ የታላቁ ህዳሴ ግድብ ምክትል ቢሮ ኃላፊ አቶ ዳዊት ምንዳዬ ክብረ በዓሉን መነሻ አድርገው እንደገለፁት ግድቡ 90% ማጠናቀቅ የተቻለ ሲሆን ቀሪውን 10% ለማጠናቀቅ 60 ቢሊዮን የሚያስፈልግ ሲሆን እንደዐይን ብሌን የምናየው የባንዲራ ፕሮጀክታችን የሆነው ህዳሴ ግድብን በማይለወጥ መርህ ጸንተን ጠላትንም አሳፍረን የእናት አባቶቻችን አደራ መወጣትና ሀገራችን ከድህነት ማላቀቅ ይኖርብናል ብለው ለታለመው ዓላማ መሳካት የአመራሩ ቁርጠኛ መሆንና የተለያዩ ዘዴዎችንም ተጠቅሞ ሀብት ማሰባሰብና ግድቡ እንዲጠናቀቅ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል ብለዋል። አቶ ዳዊት አክለውም ልደታ ክፍለ ከተማ ከዚህ ቀደም በሀብት ማሰባሰብ ላይ ሰፊ ርብርብ አድርጎ ዛሬ ላይ ለተደረሰው ውጤት የማይረሳ የትውልድ አሻራ ማሳረፍ ችሏል ለቀሪው 10% ከታቀደው በላይ ሀብት በማሰባሰብ ከበፊቱ በተሻለ መንገድ በመገኘት አስመስጋኝ ውጤት ታመጣላቹ የሚል ሙሉ እምነት አለኝ ብለዋል።

የልደታ ክፍለ ከተማ ዋና ስራ አስፈጻሚ አቶ ሰይድ አሊ በበኩላቸው እናት አባቶቻችን ደም ያፈሰሱላት ዋጋም የከፈሉላት ሀገራችን ዛሬም እንደቀደምት ጊዜያት አደራቸውን ሰጥተውን ለትውልድ የሚተላለፍ ትልቅ ቅርሳችን ሀብታችን የሆነውን ታላቁ ህዳሴ ግድባችንን አጠናቀን አደራችንን መወጣት እንዳለብንም ያስታውሱናል ያሉት አቶ ሰይድ ግድቡ ሙሉ መጠናቀቅ እንዲችል አንዱ መፍትሄ ባለሀብቱን ህብረተሰብ፣ ጤና ጣቢያዎች፣ ግብር የማይከፍለውን በማስከፈል፣አገልግሎታችንን በማዘመን፣ ት/ት ተቋማት፣የመንግስት ሰራተኞችንና ሌሎች ዘዴዎችን በመጠቀምና ተሳታፊ በማድረግ ከተማ አስተዳደሩ በሰጠው አቅጣጫ መሰረት ውጤት ማስመዝገብ ይኖርብናል ብለዋል።

የክፍለ ከተማው ምክትል ስራ አስፈፃሚና የስራ፣ ኢንተርፕራይዝና ኢንዱስትሪ ልማት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ብርሀኑ ኤኬታ ግድቡ የእያንዳንዳችን ኢትዮጵያዊያን ግዴታና ኃላፊነት በመሆኑ የሚጠበቅብንን በመወጣት በድህነትና በርሀብ የምትነሳውን ሀገራችንን ወደ እድገት እንድታቀና አንድነታችንን በማጠናከር የዜግነት ግዴታችንን መወጣት ብሎም ጥረታችንም ውጤታማ አድርገን ሀብት በማሰባሰቡም ረገድ ሙሉ ተሳታፊዎች መሆንና ህዳሴውን ሙሉ ለሙሉ ተገድቦ እንዲጠናቀቅ ማድረግ ይኖርብናል ብለዋል።

በመጨረሻም የህዳሴ ግድብ 12ኛ አመት ክብረ በዓልን መነሻ ያደረገ ሰነድ ማቅረብና 8100 ላይም አጭር መልዕክት መላክ የተቻለ ሲሆን ሀብት ለማሰባሰብ ወረዳ 08 የመጀመሪያው ሆኖ ዋንጫውን ተረክቧል።

ምንጭ ፡- የልደታ ክ/ከተማ ኮሙኑኬሽን ጽ/ቤት።
ተያያዥ መረጃዎች
© 2023 Lideta Subcity Job Creation. Designed by Markos Mulat G